ማስታወሻ፡ ከተፃፈ የከረመ
ስለ ምእራባውያን የወንጀል ችሎቶች አሰብኩ፤ ተከሳሹ ሱፉን ለብሶ ዘንጦ ነው የሚቀርበው፣ ራሱ እምቢኝ አልዘንጥም በቲሸርት እቀርባለሁ ካላለ በስተቀር፡፡ በእኛ ሃገርስ የወንጀል ችሎቶች ለምን እንደዚህ አይደረግም?… ወይ ሱፍ! ጭራሹኑ “ወንጀለኛ ነኝ” ዩኒፎርም አልብሰው ያቀርቧቸዋል፡፡ ማንም ሰው ሳይፈረድበት በፊት እንደወንጀለኛ ሊቆጠር እንደማይገባ የሚደነግገው ህገ መንግስታዊ እና ሰብዐዊ መብታዊ ነፃ ሁኖ የመገመት መብት መርህም በተደጋጋሚ ወደ አዕምሮ ይመላለሳል፡፡
ብዙም ሳልቆይ ግን ለራሴ ጥያቄዎች መልስ መስጠት ጀመርኩ፡- ያው … ማለት … እ… እ … ባይሆን ጥሩ ነበር፡፡ ለችሎት ሲቀርቡ የራሳቸውን ልብስ ለብሰው ቢቀርቡ የተሻለ ነው፡፡ ግን … ቢለብሱም ያን ያህል ጉዳት የለውም፡፡ በምዕራቡ አለም (የኮመን ሎው የህግ ስርዓት በሚከተሉ አገሮች ) ወንጀለኛ ነው ወይስ አይደለም፣ ጥፋተኛ ነው ወይስ አይደለም የሚለው ዳኝነት የሚሰጠው የህግ ትምህርት በሌላቸው እማኝ ዳኞች (ጁሪ) ነው፤ በመሆኑም አለባበስ ብሎም አጠቃላይ የተከሳሹ ገፅታ ተፅዕኖ ሊያሳድርባቸው ይችላል፡፡ በእኛ ሃገር ግን ፍርድ የሚሰጠው የህግ ትምህርት እና ልምድ ባላቸው ዳኞች ነው…፡፡ ስለዚህ ቢጫ ወይም ቀይ ዩኒፎርም መልበሳቸው ዳኞቻችን ላይ ተፅዕኖ የለውም ብዬ ደመደምኩ፡፡
የማልደብቃችሁ ነገር ግን ይህን ቢጫ ወይም ቀይ ዩኒፎርም የለበሱ እስረኞችን ስመለከት በዚህ መንገድ ለችሎት የማቅረቡ ጉዳይ ህሊናዬ እና አእምሮዬ እሰጣ እገባ ውስጥ እንዲገቡ ሳያደርጋቸው አያልፍም፤ እንዴት እንዲህ ይደረጋል?… ምን ችግር አለው? … ባያዝ?… ዳኛማ በልብስ ባያዝድ አይሆንም፣ ጁሪ መሰለህ? ቢያንስ እስኪፈረድባቸው፣ ቢያንስ ለሞራላቸውስ? … ነፃነታቸውን አጥተው ስለሞራል? … ከአካላዊ እስር አእምሯዊ እስር አይከፋም ብለህ ነው? ….
የህግ ትምህርት እና ልምድ ያላቸው ዳኞች ናቸው ጉዳዩን የሚመለከቱት… እፅናናለሁ፡፡
————————–
ማልኮም ግላድዌል የፃፈውን ድብቁን የአእምሯችንን ክፍል የተመለከተ መፅሀፍ አንብቤ እንደጨረስኩ ግን “የህግ ትምህርት እና ልምድ ያላቸው ዳኘች እኮ ናቸው!” የሚለው ማፅናኛዬ በንኖ ጠፋ፡፡
ማልኮም ግላድዌል ጥሩ ፀሃፍያን ጥቀስ ብባል ከምዘረዝራቸው ስሞች ውስጥ እንደሚኖር በእርግጠኛ ልናገርለት የምችል ግሩም ፀሃፊ ነው፡፡ ከፃፋቸው መፅሃፍት ውስጥ አራቱን – the tipping point, outliers, blink እና David and Goliath – አንብቤለታለሁ፡፡ ቢጫ ወይም ቀይ ዩኒፎርም ለብሰው ችሎት ስለሚቀርቡ ተከሳሾች “የህግ ትምህርት እና ልምድ ያላቸው ዳኘች እኮ ናቸው!” ጉዳያቸውን የሚያዩላቸው የሚለው ማፅናኛዬን እንደ አንቦ ውሃ የበተነው ግን Blink – the power of thinking without thinking የሚለው መፅሃፍ ነው፡፡ በዚህ መፅሃፉ ውስጥ ድብቁ የአእምሯችን ክፍል ሳያሳውቀን “አስቦ” እንዴት እንደሚወስንልን እና ይህም መልካም እና ጥሩ ጎኖች እንዳሉት አብራርቷል፡፡ በርካታ እውነተኛ ታሪኮችን እና ጥናታዊ ፅሁፎችንም ተጠቅሟል፡፡ ድብቁን የአእምሮ ክፍል ባለመጠቀም ስላጋጠሙ ችግሮች/ሽንፈቶች/ስህተቶች ብሎም ደብቁን የአእምሯችንን ክፍል ለብቻው በመጠቀም ስለተፈጠሩ ስህተቶች እጅግ መሳጭ በሆነ አተራረክ ያስነብባል፡፡
ድምዳሜው? ፀሃፊው ጉዳዩ ውስብስብ በመሆኑ እየፈራ እየቸረ በቀን ተቀን ህይወታችን ስለሚያጋጥሙን ውሳኔዎች እና ምርጫዎች ሲግመንድ ፍሮይድ ወደ ደረሰበት ድምዳሜ የተቃረበ ድምዳሜ ላይ ደርሷል፤ ባጠቃላይ ግን ድምዳሜው የቄሳርን ለቄሳር የአምላክን ለአምላክ ወደሚለው ያደላ ነው፡፡ የሆነ ሆኖ የስግመንደ ፍሮይድ አቋም ግን የሚከተለው ነው፡- “When making a decision of minor importance, I have always found adventurous to consider all the pros and cons. In vital matters, however, such as the choice of a mate or a profession, the decision should come from the unconscious, from somewhere within ourselves. In the important decisions of personal life, we should be governed, I think, by the deep inner needs of our nature.”
—————————
ማልኮም የሃገሩን የፍትህ ስርዓት፣ በተለይ ወንጀል የፍትህ ስርአትን በተመለከተ ግን ግልፅ መደምደሚያ ላይ ደርሷል፡- “I think that the accused in a criminal trial shouldn’t be in courtroom.” ይህን ሃሳቡን በሃርቫርድ ህግ ትምህርት ቤት ባደረገው ንግግር ላይ ሲያቀርበው የአፈፃፀሙን አስቸጋሪነት በተመለከተ ካልሆነ ምንም ተቃውሞ አልገጠመውም፡፡ ማልኮም ግላድዌል እዚህ መደምደሚያ ላይ የደረሰው ድብቁ የአእምሯችን ክፍል በፍትህ ስርዓቱ ውሳኔ አሰጣጥ ላይ ከባድ ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ስለገባው ነው፡፡
የእኔን ትኩረት የሳበውም ይህ ነው፤ የእኔን ትኩረት ይበልጥ የሳበው ድብቁ አእምሯችን ሞያተኛ የተባሉ ሰዎችን እንኳን ሲያሳስት እንደኖረ ያመላከተበት የመፅሃፉ ክፍል ነው፡፡ እንደምሳሌ የተነሳው የክላሲካል ሙዚቃ አለም ነው፡፡ በክላሲካል ሙዚቃ ኦርኬስትራ ውስጥ የሴት ሙዚቃ ተጫዋቾች ብዛት 5 በመቶ ብቻ ነበር፡፡ ሴቶች በሞያተኛ ፈታኞቻቸው ፊት ቀርበው ይፈተናሉ፣ ይወድቃሉ፤ የሚያልፉትም ቢሆን “የሴት” ተብለው ለሚታሰቡ እንደ ቫዮሊን ላሉ መሳሪያዎች ተጨዋችነት ነው፡፡ ፈተናው የሚሰጠው ልክ እንደ አሁኑ ሳይሆን ተፈታኙ መድረክ ላይ በግልፅ እየታየ መሳሪያውን ለዳኞች በመጫወት ነበር፡፡ ሴቶች ይወድቃሉ፡፡ በአሁኑ ዘመን ግን ምርጫው የሚደረገው ዳኞቹ እና ተፈታኙ ሳይተያዩ፣ ዳኞቹ ተፈታኙ ሙዚቃውን ሲጫወት በመስማት ብቻ ነው፤ ለምርጫው መሰረት ሙዚቃው እና ሙዚቃው ብቻ ናቸው፡፡ “አይ ነገር ማንዛዛት ዳኞቹ እኮ የሙዚቃ ትምህርት እና ልምድ ያላቸው ሞያተኖች ናቸው” አላችሁ? ልክ እኔ ስለሃገራችን የወንጀል ችሎት ዳኞች እንዳልኩት?
ለመጀመሪያ ጊዜ ሙዚቀኞች እና ዳኞች ሳተያዩ ሙዚቃውን በመስማት ብቻ የሙዚቃ ተጫዋቾች ምርጫ በተደረገ ወቅት የሚፈለገው አራት ሙዚቀኛ ነበር፡፡ በዳኞቹ እና በተወዳዳሪዎቹ መካከል መጋረጃ ተደረገ፤ ዳኞች እና ተወዳዳሪዎች ሳይተያዩ፣ ተፈታኞቹ የሙዚቃ መሳሪያዎቻቸውን ተጫወቱ፤ ዳኞቹም ውጤት ሰጡ፡፡ ምን የሆነ ይመስላችኋል? አራቱም ያለፉት ተወዳዳሪዎች ሴቶች ነበሩ፡፡ አጋጣሚ ይሆን? በፍፁም፡፡ የክላሲካል ኦርኬስትራ ተጫዋቾች ምርጫ ዳኞችን በመጋረጃ ሸፍኖ መደረግ ከጀመረ በኋላ የሴት ክላሲካል ሙዚቃ ኦርኬስትራ ተጫዋቾች ቁጥር ከ5 በመቶ ወደ 50 በመቶ አካባቢ አደገ፡፡ ታዲያ ይህ አጋጣሚ ነው? በፍፁም፡፡ አያችሁ በፊት የሙዚቃ ትምህርት እና ልምድ ያላቸው ዳኞች ይፈርዱ የነበረው በጆሯቸው ሳይሆን በአይናቸው ነበር፡፡
መልእክቱ፡- ድብቁ የአእምሮ ክፍላችን ሞያተኞችም ላይ ሳያውቁት ተፅዕኖ ሊያሳድር ይችላል፡፡ የሃገራችን የወንጀል ችሎት ዳኞችም እንደ ክላሲካል ሙዚቃ ኦርኬስትራ ዳኞች በጆሯቸው ሳይሆን በዐይናቸው ሊፈርዱ ይችላሉ ማለት ነው፡፡
በፍርድ ቤት ግቢ ውስጥ ስትመላለሱ ያንን ቢጫ ወይም ቀይ የለበሰ እስረኛ ስትመለከቱ ምንድን ነው ወደ አእምሯችሁ የሚመጣው መጀመሪያ ቃል? “ወንጀለኛ”! ወይም መሰል ቃል አይደለም? ምንድን ነው ወደ አእምሯችሁ የሚመጣ የመጀመሪያው ጥያቄ? “ምን ወንጀል ሰርቶ ወይም ሰርታ ይሆን?” የሚል አይደለም? የህግ ባለሞያ ብትሆኑም ጭምር! ማንም ሰው ካልተፈረደበት በቀር እንደ ንፁህ ይቆጠራል የሚለው መርህ ጠፍቶባችሁ ነው? በእርግጠኝነት አይደለም፡፡ ድብቁ የአእምሯችሁ ክፍል ተደብቆ በሚሰራው ስራ ምክንያት እንጂ!
ማልኮም ግላድዌል በሃገሩ ጥቁሮች በወንጀል ችሎቶች የሚደርስባቸውን መድሎ በተመለከተ የሂውማን ራይትስ ዎችን ሪፖርት በመጽሃፉ ላይ አሰፈረ እና እንዲህ አለን፡- “Justice is supposed to be blind. It isn’t.”
ታዲያ ፍትህ ዐይኗን ጨፍና ልትሰራ ሲገባ ዐይኗን ልትገልጥ አትችልም? ዳኛስ በድብቁ የአእምሮው ክፍል ተፅዕኖ ውስጥ ሊወድቅ አይችልም? ምነው ረሳችሁት እንዴ? ዳኛዋም እኮ ሰው ነች? ህግም ብትማር ሰው እኮ ነች? ድንገት ያዩት ቢጫ ወይም ቀይ ዩኒፎርም የለበሰን እስረኛ በተመለከተ መጀመሪያ ወደ አእምሮዎ ሚመጣው ሃሳብ “ወንጀለኛ” የሚል ከሆነ ይህች ዳኛስ ልክ እንደ እርስዎ በድብቁ አእምሮዋ ተፅዕኖ ስር ሆና “ወንጀለኛ” የሚል ታፔላ ውስጥ ውስጧን ልትለጥፍበት አትችልም?
በነገራችን ላይ ቆም ብለን ግልጹን የአእምሮ ክፍላችንን ተጠቅመን አተያየታችንን ልናስተካክል እንችላለን፤ ገና መች ተፈረደበት እና ልንል እንችላለን፤ ችግሩ ግን ንቁ ካልሆንን ራሳችን በንቁው አእምሮ እያሰብን ይሆን ወይም ድብቁ አእምሯችን ተደብቆ እያሰበልን መለየት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡ ምናልባት ድብቁ አእምሯችን ተሳስቶ ለሰጠን ተሳሳተ ድምዳሜ በንቁው አእምሯችን ድምዳሜውን ተገቢ ለማድረግ አሳማኝ ምክንያት ስንፈልግ እንገኝ ይሆናል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ሳያውቀው በድብቁ አእምሮው ተፅዕኖ ስር የወደቀ ባለሞያ በሞያው ጉዳይ ከሌላው ሰው በተሸላ ድብቁ አእምሮ (unconscious mind) ለሰጠው ድምዳሜ በንቁው አእምሮው (conscious mind) አሳማኝ መሳይ መከራከሪያዎች የማቅረብ አቅሙ ይጨምራል ማለት አይደለም? “አደጋ ነው!” አለች …
——————–
እናስ? ማልኮም ግላድዌል በመፅሃፉ መደምደሚያ ይህን አለ፡- “This is the real lesson of Blink: It is not enough simply to explore the hidden recesses of our unconscious. Once we know about how the mind works – and about the strengths and weakness of human judgment – it is our responsibility to act.”
ቢጫው ወይም ቀዩ ዩኒፎርም እዛው ማረሚያ ቤት ውስጥ ለአስተዳደርም ምቹነትም ሆነ ለንጽፅህና ወይም ለሌላ ምክንያት ያስፈልግ ይሆናል፡፡ይሁን፡፡ እስረኞች ቸሎት ሲመጡ ግን ይቅር፡፡ የራሳቸውን ልብስ ይልበሱ፡፡ ለዳኞቻችንም ተጨማሪ የማያውቁት ፈተና አንፍጠርባቸው፡፡
credit for pictures:
https://www.flickr.com/photos/cgc/6605660
https://commons.wikimedia.org/wiki/File:Prisoner_in_belly_chain_02.jpg
https://negativespace.co/to-do-list/
Comments
Post a Comment