For the food by which we live, and for the law by which we live in peace, may Lord make us truly thankful.
Ven Thomas Barfett, Lay Sheriff of London’s Chaplain July 1977
የህግ አስፈፃሚ መሆኑን ከስሙ መግለጫ መረዳት የምንችለው ይህ ግለሰብ
ለአምላኩ ሲፀልይ ወይም የምስጋና ፀሎቱን እንዴት ብሎ እንደሚያቀርብ ሲገልፅ ነው “በህይወት እንቀጥል ዘንድ ምግብን እንዲሁም በሰላም
እንኖርበት ዘንድ ህግን ስለሰጠን ጌታ ከልብ የተመሰገነ ይሁን” በማለት የተናገረው፡፡ ይህ ሰው ህግን ከምግብ ጋር አስተካሎታል፡፡
ደግሞም እውነታ አለው፤ የተረጋጋ ህይወት እንዲኖረን ህግ እና ስርአት የግድ አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ለምን? ነጋድራስ ገብረ ህይወት
ባይከዳኝ ተናገሩት ተብሎ የሚዘከርላቸው አባባል ወይም ብሂል ምላሹን የያዘ ይመስለኛል፡፡ እንዲህ አሉ፡- “በህግ ከማይኖር ትልቅ
ባለብዙ ህዝብና ሠራዊት አገር፣ በህግና ሥርዓት የምትኖር ትንሽ ከተማ ቁም ነገር ትሰራለች፡፡”
የህግ ምንነት ተመራማሪ የሆኑት ሮናልድ ዶርኪን Law’s Empire በተባለው መፃሃፋቸው መግቢያ ላይ ህግን ጥሩ
አርገው ገልፀውታል፡፡ “We live in and by the law. It makes us what we are: citizens and
employees and doctors and spouses and people who own things. It is sword,
shield, and menace: we insist on our wage, or refuse to payout rent, or are
forced to forfeit penalties, or are closed up in jail, all in the name of what
our abstract and ethereal sovereign, the law, has
decreed.” በህግ እና በህግ ውስጥ እንኖራለን፡፡ የሆንነውን እንድንሆን አድርጎናል፡፡ ንብረት ኖሮን ብንኩራራበት፣ የወደዳትን
አይቶ ሚስት ቢያደርጋት አሊያም የወደደችውን ባሏ ብታደርግ፣ ተቀጣሪ ብንሆን፣ ተምሮ ዶክተር ቢኮን፣ እንደ ዜጋ የዜግነት መብቱን
ለመጠየቅም ቢፈልግ ሁሉ በህግ ይሆናል፡፡ ባለንብረት፣ ባልና ሚስት፣ ሰራተኛም ሆነ ዜጋ የሚያደርገን ህግ ነው፣ ሲፈልግ ጋሻ ሲፈልግ ሰይፍ ሆኖ ካስፈለገ እያስፈራራ፡፡ቀጣሪያችንን ደሞዜን አምጣ ልንለው ወይንም እምቢኝ የቤቱን ኪራይ አልከፍልም እንድንል የሚያስችለን አልያም ቅጣት
አይገባኝም ስንል ነፃነታችንን የሚያውጅልን ወይም ወይህኒ የሚቆልፍብን ያው እሱው ሉዐላዊው ህግ ነው፣ ሊለን ነው ዶርኪን የፈለገው፡፡
ህግን ሉዐላዊ አለው አይደል?
ህዝቡ ሉአላዊ ነው ተብሎ በሚደሰኮርበት አለማችን ህግን ሉዐላዊ ማለቱ ይገባል?ይህን ጥያቄ ሳነሳ ነገስታት አንባገነን የነበሩበትን
ጊዜ አሰብኩ እና የእንግሊዝ የፓርላማ ሰው፣ የህግ ባለሞያ እና የህግ ምሁር የነበረውን ሰር ኤድዋርድ ኮክን በተመለከተ አንድ ፀሃፊ
ያሰፈሩትን አስታወስኩ፡፡ ፀሃፊው የሚከተለውን አተቱ፡- “[በእንግሊዝ] ኤልሳቤጥም ሆነች ጀምስ ባለሙሉ ስልጣን ነገስታት ነበሩ፡፡
በጣም ኃይለኞችም ነበሩ፡፡ ታዲያ ጀምስ ከኮክ ጋር ስለ ህግ ልዕልና የተጧጧፈ ንትርክ ይጀምራል፡፡ በአንዱ ወቅት ኮክ ጀምስን እንዲህ
ይለዋል ‹ግርማዊ ሆይ ግርማዊ ሰውነትዎ በተቀዳጀው ንጉሳዊ ስብን ከማንኛውም ተገዢዋ በላይ ነው፡፡ ስለሆነም ይህ ግርማ፣ ዙፋን
እና ንጉሳዊ ስብን ከህግ በታች ነው፡፡ ምን ጊዜም ቢሆን ከህግ በላይ ሊሆን አይችልም› አለዋ! ንጉሠ ነገስቱም ከእኔ በላይ ፈጣሪ
አምላክ ብቻ ነው የሚል ስለነበር ኮክን በዚህ አባባሉ አኩርፎት ለብዙ ዓመት በሁለቱ መካከል የከረረና የተወጠረ ሙግትና ትግል ቀጠለ፡፡
ኮክም በንጉሠ ነገስቱ እንደተከበረ፣ ሳይዋረድ እና ሳይንገላታ ለዕለተ ሞቱ በቃ፡፡” ከዚህ ማስተዋል እንደሚቻለው ሉአላዊ ነን የሚሉ
አንባገነን ነገስታት በነበሩበት ጊዜም ከእነሱ በላይ ህግ ሉዐላዊ ነው ተብሎ ተነግሯቸዋል፤ እውነታም አለው፡፡
ዘመናት አለፉ፣ የዘመናት
ማለፍ ከደም መፋሰስ ጋር ተደምሮ ሉአላዊነት የህዝብ ነው ተባለ፡፡ ግን እዚህ ላይ አንድ የሚያደንቀኝ ጥያቄ አለ፡፡ ለመሆኑ ህዝብ
ማን ነው? አግኝታችሁ አናግራችሁት ታውቃላችሁ? “ህዝብ”! ብቻ እስቲ ይህን ተወት እናርገው እና ሉአላዊው ህዝብ ነው ብለን እንለፍ፡፡
ግን ህዝብ እንዴት ሉዐላዊ ሊሆን ቻለ? የህዝብ ሉአላዊነት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ባህል አይደለም፣ የቅርብ ጊዜ ክስተት እንጂ፡፡
እናስ እንዴት ህዝብ ሉዐላዊ ሊሆን ቻለ? ጥያቄውን ጠበብ ላድርገው እና እንዴት የኢትዮጵያ ህዝብ ሉዐላዊ ሊሆን ቻለ? ህገ መንግስቱ
ሉዐላዊነት የህዝብ ነው ስላለ አይደለምን? ነው እነጂ! ህገ መንግስቱ
ደግሞ ህግ ነው፤ ስለሆነም ለህዝቡ ሉዐላዊነትን የሰጠው ህግ ነው ማለት ነው፡፡ እንግዲያውስ ህግ ሉዐላዊነትን ሰጥቶ ሉአላዊ ቢባል
ይበዛበታል፤ ምናልባት ቢያንሰው እንጂ፡፡
ድምዳሜው ህግ አስፈላጊ ነው የሚል ነው፡፡ እርግጥ ነው አብዛኛው የህግ ክፍል ብዙሃኑን የሚመራ ነው፡፡ አብዛኛው የህግ ክፍል ብዙሃኑን የሚመራ እና በሰላማዊ መንገድ ለመኖር ወሳኝ ቢሆንም የህግ ባለሞያ ያልሆነው አብዛኛው ህዝብ ግን ከህጉ ጋር ያለው ትውውቅ አነስተኛ ነው፡፡ በተለይ በገጠር የሚኖረውን ህዝብ ስናነሳ የዚህ ችግር ስፋትና ጥልቀት ግልፅ ይሆናል፡፡ ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ እንደ ቀልድ የሚነሳ በአንድ ዳኛ እና ተከሳሽ መካከል የተደረገ የቃላት ልውውጥን ልጠቅስ እወዳለሁ፡፡ተከሳሹ ዶሮዎች ሰርቀሃል ተብሎ ዳኛው ፊት ይቀርባል፡-
ዳኛው ለተከላካዩ(ተከሳሽ)(defendant): “ይህ የክስ ቻርጅ የዶሮ ስርቆትን የተመለከተ ነው፡፡ አንተ ተከላካዩ(defendant) ነህ?”
ተከላካዩ (defendant) ፡ “አይደለሁም ጌታዬ፣ እኔ ዶሮዎቹን የሰረቅሁት ሰው ነኝ፡፡”
ይህ በመጠኑ ፈገግ የሚያሰኝ
የቃላት ልውውጥ ሊኖር የቻለው ተከሳሹ የዳኛውን ቃላት ለመረዳት ባለመቻሉ ነው፡፡ ለእሱ “ተከላካይ” ማለት ስርቆቱ እንዳይደረግ
የተከላከለ ግለሰብ ነው፤ እሱ ግን “ሌባ” ተብሎ ነው ችሎት የቀረበው፡፡ ለማሳቅ በታቀደ ቀልድ ላይ ብቻ ሳይሆን በዕውነታም ህጉ
ሊገዛው ለታሰበው አብዛኛው የህብረተሰቡ ክፍል ባይተዋር ነው፡፡
በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ
የህግ ትምህርት ቤት መምህር የነበሩት በዩ ኤስ ኤ የአላባማ ዩንቨርስቲ የቻርልስ ኦ ስቶክስ የህግ ፕሮፌሰር እና የአንትሮፖሎጂ
ፕሮፌሰር (Charles O. Stokes Professor of Law and Professor of Anthropology,
University of Alabama, USA) የሆኑት ኖርማን ጄ ሲንገር በአንድ ወቅት ያጋጠማቸውን አይኔን የገለጠልኝ ድርጊት ያሉትን
ክንውን እንደሚከተለው አስፍረውታል፡- The case I watched in the courtroom involved a boundary
dispute between two neighbors. Surprisingly, both parties were unhappy about
the court decision. The person who lost the case was sad because the decision
involved a fine of 35 birr. The woman who obtained a favorable decision was
also unhappy because the penalty of the fine (payable to the state) did not
resolve her problem. She had come to the wrong (criminal) court in the first
instance, because when she filed a compliant at a police station she thought
that proceedings which ensued would solve her problem. And now she had to go
again to a civil court regarding her border demarcation compliant. ( Mizan Law
Review Vol. 2 No. 2 page 340) ፕሮፌሰሩ የተመለከቱት ሁለቱም ወገኖች ያልተደሰቱበት የድንበር ግጭትን የዳኘ ፍርድ
ቤትን ውሳኔ ነበር፡፡ የተፈረደበት ወገን መበሳጨቱ አይደንቅም 35 ብር ተቀጥቷልና፡፡ የተፈረደላቸው ሴትዮም ግን አልተደሰቱም ባላጋራቸው
መቀጣቱ እና 35 ብር ለመንግስት መግባቱ ለእሳቸው ምን ያደርግላቸዋል? ችግራቸው እኮ አሁንም አልተፈታም! እኒህ ሴት መጀመሪያውኑ
የሄዱት የወንጀል ችሎት ነው፣ ለፖሊስ በማመልከት፡፡ ያጡትን መሬት መልስው ለማግኘት ሌላ የፍትሃ ብሄር ክስ መመስረት ይጠበቅባቸዋል፡፡
የፕሮፌሰሩ አገጣሚ ህጉ እና
ስርአቱ ከህብረተሰቡ ጋር ምን ያህል እንደተራራቁ ፍንትው አርጎ የሚያሳይ ነው፡፡ ይህ ታሪክ ከተፈፀመ አመታት ቢያልፉም አሁንም
ከህግ ባለሞያዎች፣ ከፍርድ ቤት አካባቢ ከማይጠፉ ሙግት ወዳጆች ወይንም ደጋግመው ፍርድ ቤት እንዲሄዱ ከተገደዱ በስተቀር አብዛኛው
ሰው ህግና ስርአቱን አያውቅም፡፡ እዚህ ላይ ግን ሁሉም ሰው ጥልቅ የህግ ዕውቀት ይኑረው ማለቴ አይደለም፣ መሰረታዊ እንጂ፡፡
ጠቅለል አድርገን ስንመለከተው
ህጉ ሊመራው ከሚገባው ህዝብ ጋር የተራራቀ ነው ብለን መደምደም ይቻላል፡፡ ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ አይነት ማለት ነው፡፡
“ህግ ቦሌ ህዝብ ጉለሌ” ያለንበትን ሁኔታ ጥሩ አርጎ የሚገልፅ ሃረግ መሰለኝ፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ በህዝቡ እና፣ በህጉና በስርዕቱ
መካከል ቅራኜ ይፈጥራል፡፡ እዚህ ላይ አንድ ያነበብኩት ታሪክ ታዝ አለኝ፡- “አንዲት ወፈር ያሉ ደልዳላ ሴትዮ ከችሎት አዳራሽ
ባለጉዳይ ከሚቀመጥበት አካባቢ ተነስተው በመሄድ ሰብሳቢው ዳኛው ከሚቀመጥበት ባዶ ወንበር ላይ ቁጭ አሉ፡፡ ሰዉ ሆሆ! ብሎ ሲስቅ
ሴትዮዋ ‹ወንበሩ ይመቻል ምን ያቃችኋል› ብለው በመመለስ እንደገና አሳቁት፡፡ ቀጥሎም ፖሊሱ፣ ተላላኪው ከወንበሩ ይነሱ ክልክል
ነው እያሉ እንዲነሱ ሲጠይቋቸው ‹ሰዎቹ እንደሆነ አልሰሩበት ምን አለ እኔ ብቀመጥበት› ብለው መለሱ፡፡ (ወንበር ነሐሴ 2001
ገፅ 76) ሴትየዋ ቅሬታቸውን እየገለፁ ነው! እንዲህ አይነቱ ቅሬታ
በተለያየ ምክኒያት ሊመጣ ቢችልም በተወሰነ መጠን ያለመተዋወቅ ችግርም ነው - ህገ ስርዐቱ ከህዝቡ፡፡ በዚህ ረገድ አስፈፃሚ
አካላት እና የመገናኛ
ብዙኃን ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባን ድምዳሜዬ ነው፡፡
ከተፃፈ የሰነበተ
picture credit:
https://pxhere.com/en/photo/668262?utm_content=shareClip&utm_medium=referral&utm_source=pxhere
Comments
Post a Comment