“ሰው
ከተወለደበት ቀን አንስቶ እስከ ሞተበት ቀን ድረስ የህግ መብት አለው፡፡”
የፍትሃ ብሄር ህግ ቁጥር 1
አምስት መፅሃፍትን፣ 3367 ድንጋጌዎችን አካቷል፣
ሚያዚያ 27 ቀን 1952 ዓ.ም ታውጆ ከመስከረም 1 ቀን 1953 ጀምሮ ተፈፃሚ የተደረገው አብዛኛው ክፍሉ አሁንም ተፈፃሚ የሆነው
የፍትሃ ብሄር ህጋችን በርካታ ህጎችን ያቀፈ የህጎች ስብስብ ነው፡፡ በውስጡ ከያዛቸው መካከል የውርስ ወይም የአወራረስ ህግ ይገኛል፡፡
በሁለተኛው መፅሃፍ አንቀፅ አምስት ውስጥ ከቁጥር 826 እስከ 1125 ድረስ ያሉት 299 ቁጥሮች የውርስ ጉዳይን የሚደነግጉ ናቸው፡፡
ውርስ ማናችንንም ሊያጋጥመን የሚችል ጉዳይ ነው፡፡ የውርስ ህግ ክፍል ባይሆንም ውርስ የተሰኘው ፅንሰ
ሃሳብ እንዲኖር መግቢያዮ ላይ ያሰፈርኩት ድንጋጌ ትልቅ ቦታ አለው፡፡ ለዚህ ነው ብዙ ጊዜ የሃገራችን የህግ ምሁራን የውርስ ህግን
ለማብራራት ሲነሱ ከዚህ ቀጥር የሚጀምሩት፡፡ የትኛውም ሰው ከተወለደበት ቀን ጀምሮ ባለመብት ነው፡፡ በተለያየ መልኩ የተለያዩ መብቶች
እና ግዴታዎች ይኖሩታል፡፡ ሃገራችን የተቀበለቻቸው የተለያዩ ዓለም አቀፍ ህግጋትም መብቶችን ይሰጡታል፡፡ ከእነዚህም መካከል የሚከተሉት
ይገኙበታል፡-
UDHR
(UNIVERSAL DECLARATION OF HUMAN RIGHTS)
Article
17
1.
Everyone has the right to own property alone
as well as in association with others.
በዚህ ድንጋጌ መሰረት የትኛውም ሰው ከሌሎችም ጋር ሆነ ለብቻው የራሱ ንብረት የማፍራት መብት
አለው፡፡ ግን ንብረቱ ከየት ይመጣል? መልሱን ICESCR (INTERNATIONAL COVENANT ON ECONOMIC, SOCIAL
AND CULTURAL RIGHTS) እንደሚከተለው ይሰጣል፡-
Article
6
1.
The states parties to the present covenant
recognize the right to work, which includes the right of everyone to the
opportunity to gain his living by work which he freely chooses or accepts will
take appropriate steps to safeguard this right.
ይህ የማስገደድ አቅም ያለው ቃልኪዳን ለሰዎች የመስራት እና የስራቸውን ውጤት የማግኘት መብት
አጎናፅፏቸዋል፡፡ እነዚህ መብቶች ለኢትዮጲያውያንም ይሰራሉ፡፡ ህገ መንግስቱም ቢሆን በአንቀፅ 40 ንዑስ አንቀፅ 1 እና አንቀፅ
41 ንዑስ አንቀፅ 2 ላይ እነዚህ መብቶችን ይጠብቃል፤ “ማንኛውም ኢትዮጲያዊ ዜጋ የግል ንብረት ባለቤት መሆኑ/ መሆኗ ይከበርለታል/
ይከበርላታል፡፡” እና “ማንኛውም ኢትዮጲያዊ በሀገሪቱ ውስጥ በማንኛውም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የመሰማራትና ለመተዳደሪያው የመረጠውን
ሥራ የመስራት መብት አለው፡፡” በማለት፡፡
አንዲት ግለሰብ የመስራትና የስራዋን ውጤት የማግኘት መብት ካገኘች፤ አነሰም በዛም ንብረት
ማፍራት ችላለች ማለት ነው፡፡ ንብረቷን ደግሞ ሌላ ጉልበተኛ እንዳትቀማት የንብረት መብቷ ተጠብቋል፡፡ በዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችና
ቃልኪዳኖች እንዲሁም በህገ መንግስቱ የተረጋገጡት የመስራት እና የንብረት መብቶች ውጤት ይህ ነው፡፡
አንድ ህፃን ሲወለድ እነዚህን መብቶች ያገኛል፤ መብት የሚጀምረው በውልደት ነውና፡፡ የትኛውም
ሰው ሲሞት ደግሞ የህግ መብቶቹን ያጣል፤ እርግጥ አስከሬኑን እና ክብሩን ህጉ ጥበቃ ያደርግለታል፡፡ (በዚህ መልኩ ከታሰበ ግን
እንስሳትም የተለያየ ጥበቃ ይደረግላቸዋል፡፡) ነገር ግን የግለሰቡ መሞት የንብረት መብቶቹንም ይገላቸዋል፡፡ ታዲያ ያፈራው የላቡ
ውጤት ማረፊያው የት ይሆናል? ይሄኔ ነው የውርስ ህግ የሚያስፈልገው፣ ለሟችም ለቋሚም ጥቅም እና ፍላጎት፡፡
ህገ መንግስቱ እንኳ በአንቀፅ 40 ንዑስ አንቀፅ 1 ላይ የንብረትን መብት ካረጋገጠ በኋላ
“ … ይህ መብት የህዝብን ጥቅም ለመጠበቅ በሌላ ሁኔታ በህግ እስካተወሰነ ድረስ ንብረት የመያዝና በንብረት የመጠቀም ወይም የሌሎችን
ዜጎች መብቶች እስካልተቃረነ ድረስ ንብረትን የመሸጥ የማውረስ ወይም በሌላ መንገድ የማስተላለፍ መብቶችን ያካትታል፡፡”
በማለት የሟች ንብረት የትም እንዳይወድቅ የማውረስ መብትን የሰጠው፡፡
ውርስ የሞተን ወይም በመጥፋቱ ምክንያት እንደሞተ የተቆጠረን ግለሰብ ወደ ሌላ ሰው ሊተላለፉ
የሚችሉ መብቶችና ግዴታዎችን የማስተላለፍ ሂደት ነው፡፡ ይህ ሄደትም ቀድሜ እንደገለፅሁት በ1952 ዓ.ም በወጣው የፍትሃ ብሄር
ህግ ውስጥ ይገኛል፡፡
በእርግጥ ሁሉም መብት እና ግዴታ ይተላለፋል ማለት አይደለም፡፡ በገንዘብ ሊተመን የማይችሉ
እንደ እውቀት፣ ሞያ እና ማእረግ ያሉ ነገሮች በውርስ ሊላለፉ አይችሉም፡፡ ሊወረሱ የሚችሉ የሚዳሰሱም ሆኑ የማይዳሰሱ ነገሮችንም
ቢሆን ለመውረስ ወራሹ ማሟላት ያለበት ነገሮች አሉ፡፡ የመውረስ አጋጣሚ ያለው ሁሉ አይወርስም፡፡ ወራሽ ለመሆን ታዲያ ምን መሟላት
አለበት?
የጥያቄው አጭር መልስ የፍትሃ ብሄር ህጉ ቁጥር 830 ላይ ይገኛል፡፡ “ለሟቹ ሀብት
ወራሽ መሆን ለመቻል በህይወት ያለ መሆንና ለወራሽነት የማይገባ አለመሆን ነው፡፡” ይላል፡፡ ከዚህ አንፃር አንድ ግለሰብ ወራሽ
እንዲሆን የመውረስ መብት ያለው ከመሆኑ ባለፈ ሁለት ነገሮች መሟላት አለባቸው፡፡ የመጀመሪያው ወራሹ ተወራሹ ሲሞት በህይወት የነበረ
መሆን ይኖርበታል፡፡ (survivorship) ተወራሹ ሲሞት በህይወት ያልነበረ ማንኛውም ሰው ሊወርስ አይችልም፡፡
ይህን ህግ በተመለከተ ግን ልዩ ሁኔታ አለ፡፡ “There is an exception to every
rule.” የሚለው አባባል እዚህ ላይ ይሰራል፡፡ ለመውረስ ከሟች ሞት በፊት በህይወት
መገኘት ግድ ነው ለሚለው ድንጋጌም ልዩ ሁኔታ (exception) አለው፡፡ ይህ ሁኔታ የሚፈጠረው የሞተው ሰው ሚስት እርጉዝ ስትሆን
ነው፡፡ በመሰረቱ የህፃኑ መብት እና ግዴታ የሚጀምረው ሲወለድ ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ ሳይወለድ አባቱ ከሞተ አባቱ ከመሞቱ በፊት
በህይወት እንዳልነበረ ስለሚቆጠር የአባቱን ንብረት ሊወርስ አይችልም የሚለው ድምዳሜ የሚያስኬድ ይሆን ነበር፤ ልዩ ሁኔታን ህጉ
ባይደነግግ ኑሮ፡፡ በዚህ ልዩ ሁኔታ መሰረት ህፃኑ አባቱን እንዲወርስ ግን በህይወት መወለድ እና ከተወለደ በኋላ 48 ሰአት በህይወት
መቆየቱ የግድ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ ሞቶ ከተወለደ ወይም በህይወት
ከተወለደ በኋላ በ47ተኛው ሰዐት ላይ ገና በወጉ ያላወቃትን አለም ጥሏት ቢሄድ አባቱን መውረስ አይችልም፡፡ በተቃራኒዉ
በህይወት ተወልዶ 48 ሰዐት ከ1 ደቂቃ እንኳን ከኖረ ግን አባቱ የሞተው እሱ ሳይወለድ ቢሆንም ወራሽ መሆን ይችላል፡፡ በእርግጥ
እሱ ራሱ ስለሞተ እናቱ እሱን ተክታ ትወርሳለች፡፡
ቀጣዩ ትኩረታችንን ልንቸረው የሚገባው የአብሮ ሟቾች ጉዳይ ነው፡፡ የአብሮ ሟቾችን በተመለከተ የፍትሃ ብሄር
ህጉ ቁጥር 832 የሚተለውን አስፍሯል፡- “ሁለት ወይም ብዙ ሰዎች የሞቱ ሲሆንና ከእነዚሁ ሰዎች መካከል በኋላ የሞተው የትኛው
እንደሆነ ለማወቅ ያልተቻለ እንደሆነ ከአብሮ ሟቾች ሰዎች ሀብት ወራሽነት ምንም ሳያገኝ የእነዚሁ ሰዎች የእያንዳንዳቸው ውርስ በመጨረሻ
እንደሞተ ዓይነት ተቆጥሮ ይወሰናል፡፡” ስለዚህ በዚህ ድንጋጌ መሰረት ማን ቀድሞ እንደሞተ ማወቅ ከተሳነን ሁሉም እንደ አብሮ ሟቾች
ተቆጥረው ማናቸውም የሌላው ወራሾች የመሆን መብታቸውን ይነጠቃሉ፡፡
አንዳንድ ወራሾች እና ተወራሾች ደግሞ በአጭር ጊዜ ልዩነት ተቀዳድመው ይሞታሉ ወይም ወራሹ የተወራሹን ንብረት
ወርሶ ወደራሱ ሳያዛውር የተወራሹን መንገድ ተከትሎ በሞት ያንቀላፋል፡፡ በዚህ ወቅት ታዲያ ምን ይበጀናል? ህጋችን መልስ ሲሰጥ
“በአንድ ውርስ ወራሽ የሆነ አንድ ሰው ከውርሱ በኋላ የሞተ እንደሆነ የወራሽነት መብቶች ለርሱ ወራሾች አስተላልፏል፡፡” ይለናል፡፡
እንግዲያውስ አያት ከሁለት ቀን በፊት ሞቶ ልጁ አባቱን ከቀበረ በኋላ ዛሬ ቢሞት የልጅ ልጅ አባቱን ወክሎ የአባቱን ድርሻ ከአያቱ
ሃብት ከሌሎች አጎቶቹ እና አክስቶቼ ጋር ተካፍሎ ይወርሳል ማለት ነው፡፡
picture credit: Jordi picart, CC BY-SA 4.0 <https://creativecommons.org/licenses/by-sa/4.0>, via Wikimedia Commons
Comments
Post a Comment