Skip to main content

ገድሎ መውረስ ይቻል ይሆን? (Is Killing to Inherit possible?)

 


“No one shall be permitted to profit by his own fraud, or to take advantage of his own wrong, or to found any claim up on iniquity, or to acquire property by his own crime.”  

                   Riggs v palmer, New York court (1889)

የጥንት ታሪክ ነው፤ግን በጣም ታዋቂ ታሪክ ነው፡፡ አሜሪካ ኒው ዮርክ ከተማ ውስጥ በ1882 (በእነሱው አቆጣጠር)ነው፡፡ ኤልመር የተባለ ግለሰብ አያቱን ገደላቸው፤ካለምንም ርእራሄ ምስኪኑን ሽማግሌ በመርዝ ገደላቸው፡፡ አያትየው ከዘመዶቻቸው ሁሉ የሚወዱት የልጅ ልጃቸው ነው መሰል አብዛኛውን ንብረታቸውን ለአቶ ኤልመር ነው የተናዘዙት፡፡አያቱ እስኪሞቱ መጠበቅ ሰልችቶት አይደለም የገደላቸው፤ተቀናቃኝ መጥቶበት እንጂ፡፡ እርጅና አጋርን መፈለግን እና ፍቅርን አይከለክልምና አያቱ ሚስት አገቡ፡፡ ልላ ተቀናቃኝ ተወዳጅ ሰው መምጣቱን ያስተዋለው ኤልመን የቀድሞውን ኑዛዜ አያቱ እንዳይቀይሩት ሰጋ፡፡ አሰበ፤ተጨነቀ፤ልያጣው የሜችለው ሃብት አይኑን አቀላው፤አንገበገበው፤አስገበገበው፡፡ አያቱን በመርዝ ገደላቸው፤ኑዛዜውን ሳይቀይሩ ሳይቀደም መቅደሙ ነው፡፡ለነገሩ እኮ ሰውየው ጭራሽ ኑዛዜያቸውንም ላይለውጡት ይችሉ ነበር፡፡

 

ከብዙ ምርመራና ክትትል በኋላ በድብቅ የሰራው ወንጀል ፀሃይ ሞቀው እና የኤልመር ወንጀል ተደረሰበት፤ፍርድ ቤት ቀረበ ከዛም ተፈረደበት፡፡አመታትንም በእስር ቤት አሳለፈ፤ፍርዱን ሲጨርስም ከእስር ተለቀቀ፡፡ይሄኔ አቶ ኤልመርዬ አይኑን ሳያሽ የአያቴን ንብረት በኑዛዜው መሰረት ልውረስ አለ፡፡

 

ባለፈው ሳምንት ውርስን ጠቅለል ባለ መልኩ እና ወራሽ ለመሆን መሟላት ስላለባቸው ነገሮች አውስተናል፡፡ባለፈው ሳምንት የፍትሃብሄር ህጉን ቁ.830 ተመስርቼ ወራሽ ለመሆን ሁለት ነገሮች መሟላት እንዳለባቸው እና የመጀመሪያው ወራሽ አወራሹ ግለሰብ ሲሞት በህይወት የነበረ መሆን እንደሚኖርበት፤ይህም በህይወት ያለ መሆን (survivorship) እንደሚባል  አብራርቻለሁ፡፡አሁን ሁለተኛው ላይ እናተኩር፡፡ የኒው ዮርኩ ታሪክ አላማም ወራሽ ለመሆን መሟላት ያለበትን ሁለተኛውን ነጥብ ለማጉላት ነው፡፡ሁለተኛው መስፈርት “ለወራሽነት የማይገባ አለመሆን” (not unworthy) ነው፡፡  

 

ወደ ኒውዮርክ ታሪክ እንመለስ፡፡ የኤልመርን ፍላጎት የተረዱት በኑዛዜው መሰረት ከኤልመር የተረፈውን ወይም ኤልመር አያቱን ቀድሞ ከሞተ ንብረቱን እንዲወረሱ ታስበው የነበሩት ሁለቱ የአያተየው ሴት ልጆች የኤልመር ደግሞ አክስቶች አይሆንም ፣እንዴት ተደርጎ አሉ፡፡ ጉዳዩም ፍርድቤት ደረሰ፡፡

 

በወቅቱ የነበረው የኒውዮርክ የኑዛዜ ህግ ኑዛዜው በህግ ፊት ዋጋ እንዲኖረው ምን ያህል እና ምን አይነት ምስክሮች እንደሚያስፈልጉ፣ የተናዛዡ የአእምሮ ሁኔታ ምን አይነት መሆን እንዳለበት፣ ተናዛዡ ሲፈልግ ኑዛዜውን እንዴት መልሶ ማስተካከል ወይም መሰረዝ እንደሚችል እና ሌሎችንም ይደንግጉ እንጂ አውራሹን የገደለ የኑዛዜ ወራሽ በእርግጥ እንዲወርስ ይፈቀድለት አልያስ ይከልከል የሚለውን ጥያቄ በተመለከተ ግን ምንም የሚለው ነገር የለም፡፡ ስለዚህም የኤልመር አክስቶች አባታችንን ገድሏል በመሆኑም እንዲወርስ ሊፈቀድለት አይገባም ብለው ሲከራከሩ የኤልመር ጠበቃ ደግሞ እስኪ የሚከለክል ህግ አሳዩኝ ኤልመር የትኛውንም የኑዛዜ ውርስ ህግን ስላልጣሰ ሊወርስ ይገባዋል ብሎ ወገቡን ይዞ ተከራከረ፡፡ ዳኞቹ ምን ይዋጣቸው?



የእኛ አገር ዳኞች ይህ ችግር የለባቸውም፡፡ በ1952 ዓ.ም (በአውሮፓውያን አቆጣጠር በ1960ዓ.ም) የታወጀው የፍትሃ ብሄር ህግ ይህን ጉዳይ በተመለከተ እንደ እነኤልመር ዘመን የኒውዮርክ ህግ ዝም ማለትን አልመረጠም፡፡ እንደሚከተለው ይላል፡-

ቁ. 838፡፡ ያልተገባ ስለመሆን  (1) ወንጀሎች ወይም ቅጣቶች

ሟቹን ለመውረስ የማይገባ ነው ተብሎ የወራሽነት መብት የሚያጣ

ሀ) ሟቹን ወይም የሟቹን ወደታች የሚቆጠሩ ተወላጅ ወይም ወደ ላይ የሚቆጠሩ ወላጆች አንዱን ወይም የሟቹን ባል ወይም ሚስት አስቦ በመግደል የተፈረደበት

ለ) በሃሰት በመሆን በመወንጀል ወይም በሀሰት ምስክርነት፣ ይህ በሀሰት መወንጀል በሀሰት መመስከር ከእነዚሁ ሰዎች መካከል በአንደኛው ላይ የሞት ፍርድ ወይም ከአስር አመት የበለጠ የፅኑ እስራት እና ቅጣትን ለማስከተል የሚያሰጋ ሆኖ የተቀጣ ማንኛውም ሰው ነው፡፡

 

የኒው ዮርኮቹ ዳኞች ተከራከሩ፣ ተጨቃጨቁ እና በድምፅ ብልጫ የሚከተለውን አሉ፡- “ it is quite true that status regulating the making, proof and effect of wills, and the devolution of property, if literally construed, and if there force and effect can in no way and  under no circumstances be controlled or modified, give this property to the murderer.” ካሉ በኋላ ነገር ግን ብለው ቀጠሉ “ all laws as well as all contracts may be controlled in their operation and effect by general, fundamental maxims of the common law. No one shall be permitted to profit by his own fraud, or to take advantage of his own wrong, or to found any claim up on his own iniquity, or to acquire property by his own crime.” በማለት እንዳይወርስ ከለከሉት፡፡

 

በእርግጥ ስለኑዛዜ አፃፃፍ፣ ስለማረጋገጥ፣ ስለውጤቶቹ እንዲሁም ስለ ንብረት ክፍፍል የሚደነግጉትን የህግ ክፍሎች ቃል በቃል ተርጉመን ተግባራዊ ቢደረጉ ንብረቶቹ ለነፍስ አጥፊው መስጠታቸው ነው፤ ነገር ግን ሁሉንም ህጎችንም ሆነ ውሎች ልንቆጣጠርበት የሚገባ መሰረታዊ የህግ መርህ አለ፡- ‹ማንም በራሱ የማጭበርበር ተግባር ትርፍ ሊያገኝ፣በራሱ ስህተት ሊጠቀም ወይም በራሱ ወንጀል ንብረትን ሊያገኝ አይችልም›ይላል በማለት በድምጽ ብልጫ ኤልመርን እንደጎመጀ ትቀራለህ እንጂ ይህን ንብረት አታገኝም ብለው ወሰኑ፡፡ሌባ ከሰረቀ በኋላ ስለሰረቅህ ይህን ያህል ጊዜ እስር ቤት ግባ የሰረቅኧው ግን ያንተ ንብረት ይሆናል እንደማይባለው ሁሉ ማለት ነው፡፡ሌባ የሰረቀውን ይቀማል፡፡   

 

እንግዲህ ወራሽ ለመሆን ሁለተኛው መስፈርት እንደ ኤልመር ለመውረስ ያልተገባ (unworthy) አለመሆን ነው፡፡በእኛ ህግ ደግሞ ያልተገባ የሚያደርገው አውራሹን መግደል ብቻ አይደለም፡፡

 

ሟቹን ጨምሮ “የሟቹን ወደታች የሚቆጠር ተወላጅ” ማለትም ልጆቹን የልጅ ልጆቹን እያለ ወደታች የሱ ተወላጅ የሆኑትን አሊያም “ወደላይ የሚቆጠሩ ወላጆችን” ማለትም አባት፣እናት፣አያት፣ቅድመ አያት እያለ በህይወት እስካሉ ድረስ ወደላይ የሚቆጠሩ ወላጆቹን ወይም የሟቹን ሚስት ወይም ባል ሆን ብሎ በፍላጎት የገደለ ወይም ለመግደል ሞክሮ ያልተሳካለት በወንጀል ተከሶ ከተፈረደበት ለመውረስ ያልተገባ ይሆናል፡፡

 

እነዚህን የተጠቀሱትን ወላጆች፣ተወላጆችም ሆነ ባል ወይም ሚስት ከ10 አመት በበለጠ ልያሳስረው(ጽኑ እስራት) ወይም በሞት ሊያስቀጣው የሚችል ወንጀል ፈጽመዋል ብሎ በሃሰት የመሰከረም የሟቹን ንብረት ለመውረስ ያልተገባ ይሆናል፡፡ለምሳሌ የእንጀራ እናቱ ጎረቤቷ በግፍ የጭካኔ አገዳደል ገድላለች ብሎ በሀሰት ፍርድ ቤት ቆሞ ቢመሰክር አባቱ ሲሞት የሱን ንብረት ለመውረስ ያልተገባ ይሆናል፡፡እዚህ ላይ ግን ትኩረት የሚሻ ነጥብ አለ፡፡እስካሁን ስዘበዝብ የነበረው ሁሉ ተፈጻሚነት የሚኖረው ድርጊቱ ሟቹ ከመሞቱ በፊት የተፈጸመ ሲሆን ነው፡፡አንድ ግለሰብ አባቱ ከሞተ በኋላ እህቱን ለመግደል ቢሞክር አባቱን ለመውረስ ያልተገባ ሊሆን አይችልም፡፡

 

ይህ ያልተገባ(unworthy) ያለመሆን መስፈርት ለህብረተሰባችን አንድነትና ሰላም የሚያበረከተው የማይናቅ አስተዋጽሆ አለው፡፡ይህንኑ በተመለከተ አበር አበበ የተባሉ ጸሃፊ የሚከተለውን ብለዋል ፡- “ለወራሽነት የማይገባ መሆን ለምን የመውረስን ችሎታን ያሳጣል?ምክንያቱም ለአውራሽ ሞት መንስሄ ለሆነ ሰው ወራሽነት መፍቀድ የማህበረሰብን ሞራል ይነካል፡፡አንድ ሰው ከራሱ ስህተት ወይም ጥፋት ተጠቃሚ መሆን የለበትም፡፡ወንጀል የሰራን ወራሽ ለወራሽነት ያልተገባ ማድረግ የወንጀል ፍላጎትን ይቀንሳል ማለትም ወራሹ ጥፋቱ ለውርስ መንስሄ ከሆነ የወንጀለኝነት ፍላጎቱ ይጨምራል፡፡በጥፋተኛነቱ ምክንያት ከውርስ ከተወገደ ግን የወንጀለኛነት ባህሪው ይቀንሳል፡፡”

 

    ይህንኑ ግብ በመያዝ ህጉ ሌሎች ሁለት ተጨማሪ ለውርስ ያልተገቡ የሚያደርጉ ምክንያቶችንም ይጨምራል፡፡የፍትሃ ብሄር ህጉ ቁ.840 የሚከተለውን ይላል፡-

ቁ.840(3) ሌሎች ምክንያቶች

በተለይ የሟቹን ለመውረስ የማይገባ ነው ተብሎ፡-

ሀ)የሟቹን ሰውነት ሁኔታ ምክንያት በማድረግ አውራሹ ከመሞቱ በፊት በአሉት በሶስት ወራት ውስጥ ኑዛዝ እንዲያደርግ፣እንዳይለወጥ ወይም እንዳይሽር የከለከለ፤

ለ)አስቦ ያለሟቹ ፈቃድ የሟቹን የመጨረሻ ኑዛዜ ያበላሸ እንዳይገኝ ያደረገ ያጠፋ ወይም ጉዳዩን በማወቅ በሃሰት ኑዛዜ የተጠቀመ የወራሽነት መብት ያጣል፡፡

 

የአማርኛው ቅጂ ሲጀምር “በተለይ የሟቹን ለመውረስ የማይገባ ነው ተብሎ” ብሎ መጀመሩ ግለሰቡ መጀመሪያውኑ ለመውረስ የማይገባ እንደሆነ እና “ሀ” እና “ለ” የተገለጹት ለመውረስ ያልተገባ ከሆነ በኋላ የፈጸማቸው እንደሆኑ ያስመስላል፡፡ነገር ግን ይመስላል እንጂ አይደለም፡፡አንድ፣እራሱ የአማርኛው ቅጂ ሲጨርስ “የወራሽነት መብት ያጣል” ማለቱ እንዲሁም የህጉ ቁጥር “ሌሎች ምክንያቶች” (other causes) የሚል ርዕስ ማግኘቱ ግለሰቡ መጀመሪያ የወራሽነት መብት የነበረው መሆኑን ከተዘረዘሩት ሁለት ምክንያቶች መካከል በአንዱ ወይም በሁለቱ ምክንያቶች ግን ያልተገባ ሊሆን እንደሚችልና ቀድሞ ባሉት ቁጥሮች ከተጠቀሱት ምክንያቶች በተጨማሪ ያልተገባ የሚያደርጉ ሌሎች ምክንያቶች መኖራቸውን የሚደነግግ እንጂ ያልተገባ የተባለ ሰው ደርቦ የሚፈጽማቸው እንዳልሆኑ ያሳያል፡፡በሁለተኛው ደረጃ ደግሞ የእንግሊዘኛውን ቅጂ መመልከት የቁጥሩን መልዕክት ይበልጥ ያጠራዋል፡፡እንዲህ ይላል፡-

Article 840  -3 other causes

Whosoever:

A) by taking advantage of the physical state of the deceased has within three months prior to the death of the latter, prevented him from making or revoking his will; or

B) has intentionally destroyed, caused to disappear or altered the last will of the deceased, without the consent knowing it to be such, shall lose capacity to succeed the decreased as unworthy.

 

የእንግሊዘኛ ቅጂ whosoever (ማንም ሰው) ብሎ ጀምሮ ድርጊቶቹን ዘርዝሮ እነዚህን ድርጊቶች ከፈጸሙ ለውርስ የማይገባ እንደሚሆን ይደነግጋል፡፡ስለዚህ የአማረኛው “በተለይ ሟቹን ለመውረስ የማይገባ ነው ተብሎ” የሚለው እንግሊዘኛው whosoever የሚለውን አሳብ ለማስተላለፍ ስለሆነ “ሀ” እና “ለ” ላይ የተጠቀሱት ተጨማሪ ማንኛውንም ሰው የማይገባ የሚያደርጉ ምክንያቶች እንጂ  ቀድሞውኑ የማይገባ የተባለ ሰው ሊፈፅማቸው የሚገባ ድርጊቶች አይደሉም፡፡ ለነገሩ ቀድሞውኑ የማይገባ የተባለን ሰው  መልሶ በዚህ ምክንያት በድጋሚ የማይገባ ነህ ማለት ትርጉም የለውም፤ከድካም ውጭ፡፡

 

በዚህም ሆነ በዚያ ግን አንድ ግለሰብ ሟቹ ከመሞቱ ከሶስት ወር በፊት የሟቹን የሰውነት ሁኔታ (physical state) ማለትም መጃጃትን ጤንነት ማጣትን፣ የአእምሮ ጉዳትን(ለምሳሌ ክሊኒካል የመንፈስ ጭንቀትን) እና በእሱ ቁጥጥር ስር የነበረ መሆኑን ተጠቅሞ እንዳይናዘዝ ወይም የተናዘዘውን እንዳይለውጥ  ወይም እንዳይሽር ያረገ ለመውርስ ያልተገባ ይሆናል፡፡ልብ ልንል የሚገባው፣ይህ ድርጊት የተፈጸመው ሟች ከመሞቱ ከ3 ወር ከ1 ቀን በፊት ቢሆን እንኳ ለመውረስ ያልተገባ አያደርገውም፡፡ ሶስት ወር ወይም ያነሰ ሲሆን ብቻ ነው የድርጊቱ መፈጸም ለመውረስ ያልተገቡ መሆንን ሊያስከትል የሚችለው፡፡ ሌላው ተጨማሪ ምክንያት ደግሞ ሆን ብሎ ከሟች ፈቃድ ውጭ ኑዛዜውን እንዲጠፋ ያደረገ (ለምሳሌ ያቃጠለ፣የደበቀ ወዘተ) ወይም የለወጠ (ለምሳሌ ፍቆ የለወጠ) ለውርሱ ያልተገባ ይሆናል፡፡ የሃሰት መሆኑን እያወቀ አንድን ኑዛዜ እንዲተገበር ያደረገ ወይም የተጠቀመበት ግለሰብም ተመሳሳይ እጣ አይቀርለትም፡፡

 

እነዚህ ተጨማሪ  ምክንያቶች ግን በዚህ   ጽሁፍ መጀመሪያ አካባቢ ቁጥር 838ን ጠቅሼ ካነሳኋቸው ምክንያቶች ጋር ሰዎችን ለውርስ የማይገቡ በሚያደርጉበት መንገድ ረገድ ልዩነት አለ፡፡ በቁጥር 838 መሰረት በመግደል፣ ለመግደል በመሞከር ወይም በሃሰት ክስ ምክንያት አንድ ግለሰብ ለውርስ የማይገባ እንዲሆን ይህንኑ በተመለከተ በፍርድ ቤት የተወሰነባቸው መሆን አለባቸው፡፡ በተቃራኒው አሁን በቁጥር 840 ላይ ያየናቸው ምክንያቶች ግን አንድን ግለሰብ ለውርስ የማይገባ ለማድረግ በፍርድ ቤት ድርጊቱን ስለመፈጸሙ የተወሰነበት መሆን ግድ  አያስፈልግም፡፡

 

አሁን ወደመጨረሻው ነጥብ ደርሰናል፡፡ ሟች ከመሞቷ በፊት ሊወርሷት ከሚችሉት መካከል አንዱ በህግ ዘንድ ለመውረስ ያልተገባ መሆኑን አስተውላ፣ “ሃጢያታችሁ ይቅር እንዲባልላችሁ ይቅር በሉ” የሚለውን መለኮታዊ ትዕዛዝ ለመፈፀም አሊያም በተፈጥሮዋ የለየላት ይቅር ባይ ስለሆነች ወይንም ‹ባሌን እንደሆነ እንኳን የገደልከው መጀመሪያውኑ ሰልችቶኝ ልገለው ምቹ ጊዜ ነበር የምጠብቀው› በሚል እኩይ መንፈስ ወይም በሌላ ምክንያት ተገፋፍታ ይቅር ልትለው ብትፈልግስ? ህጋችን ግልፅ በሆነ ፅሁፍ ይቅርታዋን እስከገለፀች ድረስ መብቷ ነው ይላል፡፡ በነገራችን ላይ ኑዛዜው የተፃፈው ለመውረስ ያልተገባ የሚያደርገው ድርጊት ከተፈፀመ በኋላ ከሆነ ደግሞ ህጉ ኑዛዜ አድራጊው ድርጊቱን ለፈፀመው ግለሰብ ይቅርታ እንዳደረገለት አድርጎ ይቆጥረዋል፡፡     




picture credit: https://www.lawblogonline.com/will-anticipating-your-succession-part-2/

Comments