መንግስት ሁሉም በሌላው ወጪ ለመኖር የሚጥርበት ታላቅ ልብ ወለድ ነው፡፡
ፍሬደሪክ ባስቲያት
‹‹ የተጣጣመ ማህበራዊ ህይወትንና
የሰው ልጅ ዕድገትን ለመቀዳጀት የሚቻለው ንብረት በግል ሲያዝና ግለሰቦች በኢኮኖሚያዊ እና በሌሎች ዘርፎች ውስጥ ለሚያከናውኑት
ተግባር በቂ ነፃነት እና ዋስትና ሲያገኙ ብቻ ነው የሚል …. አስተሳሰብ ነው፡፡›› ሲል ነው የማርክሲዝም ሌኒኒዝም መዝገበ ቃላት ለነፃዊነት ወይም ሌበራሊዝም ትርጉም የሰጠው፡፡ ከሞላ ጎደል የአስተሳሰቡን
መሰረታዊ አመለካከት ያስቀመጠ ትርጉም ነው፡፡
ነፃዊነት ወይም ሌበራሊዝም ሲነሳ
አብረው የሚነሱ በርካታ ምሁራን አሉ፤ ምንአልባት የተወሰኑት በአንባቢው
ምናብ ውልብ ብለው ሊሆን ይችላል፡፡ የዚህ ፅሁፍ አላማ ግን ስለታዋቂዎቹ የነፃዊነት አራማጆች ማውሳት ወይም ስራቸውን ማቅረብ አይደለም፤
ብዙም ስለማይታወቀው ፈረንሳዊ የነፃዊነት አቀንቃኝ ለማውሳት እንጂ፡፡ ዋልተር ኢ. ዊልያምስ የተባሉ ቨርጂንያ የሚገኘው ጆርጅ ማሶን
ዩንቨርስቲ የስነ ኢኮኖሚ ፕሮፌሰር እንኳን ስለሰውየው ዘ ሎው
የተሰኘ መፅሃፍ ያወቁት የማያውቁት ሰው መፅሃፉ በፖስታ ከላከላቸው በኋላ ነበር፡፡
ፈረንሳዊው ፍሬደሪክ ባስቲያት ይባላል፡፡
የዚህ ፅሁፍ መግቢያ ላይ ያለውን ሃሳብ የፃፈው ይህ ሰው የመንግስት ሚና እጅግ ውስን መሆን አለበት የሚል አቋም ያለው የነፃነታዊ
አስተሳሰብ አራማጅ ነው፡፡ ዘ ሎው የተባለው መፅሃፉን ያነበቡት ውስብስቡን የነፃዊነት ፍልስፍና ለተራው
ሰው ሊገባው በሚችል መንገድ ጥሩ አርጎ አስፍሮታል ይላሉ፡፡ መጣጥፉ 60 ገፅ እንኳን አይሞላም፡፡ እነሆ ይህ ከሆነ ዘንዳ እኔም
እናንብበው ብዬ ልተረጉመው እና ለኢትዮ ምህዳር አንባቢዎች ላቀርበው አሰብኩ፡፡
በተከታታይ ሳምንታት የመፅሃፉ ትርጉም የማቀርብ ቢሆንም ለዛሬ ግን ጥሩ መንደርደሪያ ይሆነናል እና ሜሪ ላንድ የሚገኘው ሎዮላ ኮሌጅ የስነ ኢኮኖሚ ፕሮፌሰር እና የሚሰስ ኢንስቲትዩት ሲንየር መምህራን አንዱ የሆኑት ቶማስ ዲሎሬንዞ ለመፅሃፉ ያዘጋጁትን መንደርደሪያ እነሆኝ፡-
ነፃነትን የተመለከተ የግል ቤተ-መፅሃፍት
ማደራጀት የፈለገ የትኛውም ሰው ዘ ሎው (The Law) የተሰኘው
የፍሬደሪክ ባስቲያትን ዘመን አይሽሬ መጣጥፍ ቅጂ ሊያካትት ይገባል፡፡ በፈረንሳዊው ታላቅ ኢኮኖሚስት እና ጋዜጠኛ ለመጀመሪያ ጊዜ
በ1850 እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ሲታተም ልክ አሜሪካ ስትመሰረት
በመስራቾቹ ምናብ ውስጥ እንደነበረው እና በአሜሪካው የነፃነት አዋጅ (Declaration of independence) እንደታወጀው
የመንግስት ዓይነት፣ የየትኛውም መንግስት ዓላማ የዜጎቹን ህይወት፣ ነፃነት እና ንብረት መጠበቅ ነው የሚል ግልፅ መግለጫ የያዘ
ነበር፡፡
ባስቲያት፣ ሁሉም የሰው ዘር ከአምላክ
የተሰጠው ‹‹የግለሰባዊነት፣ የነፃነት፣ የንብረት›› ተፈጥሯዊ መብት አለው ብሎ ያምናል፡፡ ‹‹ሰው ማለት ይህ ነው›› ሲልም ፅፏል፡፡
እነዚህ ‹‹ ከአምላክ የተሰጡ ሶስት ስጦታዎች ከሁሉም ሰው ሰራሽ ህግጋት ይቀድማሉ፡፡›› በእሱ ጊዜ ማለትም ይፅፍባቸው በነበሩት
1840ዎቹ (እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር) ሳይቀር ባስቲያት ህግ ተዛብቶ ህጋዊ ብዝበዛ (legal plunder) ሲል ለሚጠራው
ሁኔታ በመሳሪያነት እያገለገለ መሆኑ አሳስቦት ነበር፡፡ ህግ የግለሰብ መብቶችን ከመጠበቅ ፍፁም ርቆ የአንድ የዜጎች ቡድንን ለመጥቀም
በተለይ መንግስትን ለመጥቀም ሌላ የዜጎች ቡድን ያለውን መብት ለመንጠቅ አገልግሎት ላይ መዋሉ እየተበራከተ ነው፡፡ ክላሎታዊ ታሪፎችን
(ገቢ እቃዎችን ወደአገር እንዳይገቡ መከላከያ ዘዴ)፣ ማንኛውም አይነት የመንግስት ድጎማን፣ ከገቢ ጋር እያደገ የሚሄድ ግብርን
(progressive taxation)፣ የመንግስት ትምህርት ቤቶችን፣ የመንግስት የስራ ፈጠራ ፕሮግራሞችን (government
“job” program)፣ አነስተኛ ደሞዝ መጠንን የሚደነግጉ ህጎችን፣ ነፃ ማህበራዊ አገልግሎት (welfare)፣ የአራጣ ህጎችን
(በገንዘብ ብድር ላይ የወለድ መጠንን የሚገድቡ) (usury laws) እና ሌሎችንም ህጋዊ ብዝበዛዎች አውግዟል፡፡
ባስቲያት የህጋዊ ብዝበዛ አስከፊ
ውጤቶችን በተመለከተ የሰጣቸው ማስጠንቀቂያዎች በፃፋቸው ወቅት ጠቃሚ የነበሩትን ያህል አሁንም ጠቃሚ ናቸው፡፡ የህጋዊ ብዝበዛ
(legal plunder) ሥርዓት (አሁን ብዙዎች ‹‹ዲሞክራሲ›› ብለው የሚያጨበጭቡለት) ከሁሉም ሰው አእምሮ ወስጥ የፍትህ እና
የኢ-ፍትህን ልዩነት አጥፍቶታል ሲል ፅፏል፡፡ የተበዘበዙት መደቦች ከጊዜ በኋላ ወደ ፖለቲካው ጨዋታ እንዴት እንደሚገባ ይገባቸውና
መልሰው ሌላውን ሰው ይበዘብዛሉ፡፡ የሚወጡ ህግጋት በፍትህ መርሆች ሳይሆን በአረመኔ የፖለቲካ ሃይል ቅኝት ይወጣሉ፡፡
ፈረንሳዊው የነፃነት ጀግና ትምህርት በመንግስት እንደሚበከልም ተንብዩል፡፡
‹‹ከመንግስት የተሰጣቸውን የማስተማር ስልጣን›› የያዙ፣ መንግስት የተሰጣቸውን ቦታ ይቀማናል በሚል ፍራቻ ህጋዊ ብዝበዛን እምብዛም
አይተቹም፡፡
የህጋዊ ብዝበዛ ስርዓት፣ ፖለቲካ
በማህበረሰብ ውስጥ ያለውን አስፈላጊነትም እጅግ አጋኖ ያቀርባል፡፡ ይህ ደግሞ ቁጥራቸው እየጨመረ ያሉ ዜጎች ለገበያ የሚቀርብ ምርት
እና አገልግሎት በማምረት ራሳቸውን ከማሻሻል ይልቅ፣ በፖለቲካ በኩል ሌሎች ዜጎችን እንዲዘርፉ የሚያበረታታ እጅግ ጤናማ ያልሆነ
እድገት ነው፡፡ ባስቲያት ዘመናዊ
የኢኮኖሚ ባለሞያዎች ኪራይ ሰብሳቢነት (rent seeking) እና ኪራይ አስወጋጅነት (rent avoidance) እያሉ የሚጠሯቸውን ክስተቶች መተንበይ
ያስቻለው ጥበብ ነበረው፡፡ እነዚህ ሁለት ግራ አጋቢ ሃረጎች (እንደየ አጠቃቀስ ተራቸው) የፖለቲካ እርዳታን (ህጋዊ ብዝበዛን)
ለማግኘት የሚደረግ የማግባባት ስራን እና ከብዝበዛ ፈላጊዎች በደል ራስን ለመጠበቅ ታስቦ የሚደረግ ፖለቲካዊ ተሳትፎን ያመለክታሉ፡፡
(ለምሳሌ የብረት ማምረቻ ኢንዱስትሪ ከውጭ የሚገባ ብረት ላይ ከፍተኛ ታሪፍ እንዲጣል ሲወተውት ብረትን የሚጠቀሙ የተሽከርካሪ አምራቾችን
የመሰሉ ኢንዱስትሪ ደግሞ በብረት ላይ ከፍተኛ ታሪፍ እንዳይጣል መወትወቱ አይቀርም፡፡)
ዘመናዊ ኢኮኖሚስቶች ስለኪራይ ሰብሳቢነት
የሚጨነቁት በሚያስከትለው ጉዳት (opportunity cost) ምክንያት ነው፡፡ በኪራይ ሰብሳቢነት ምክንያት ነጋዴዎች ሃብትን ለሚያሳድግ፣
ምርት እና አገልግሎትን ለማቅረብ የሚያጠፉት ጊዜ እየቀነሰ መጥቶ፤ በፖለቲካው ላይ ተፅዕኖ ለማድረግ በመዶለት (ብቸኛ ውጤቱ ሃብትን
ከአንዱ እጅ ወደ ሌላው ማስተላለፍ ብቻ ሆኖ ሳለ) የሚያጠፉት ጊዜ ፣ጥረት እና ገንዘብ የበለጠ ይሆናል፡፡ ስለሆነም ህጋዊ ብዝበዛ ጥቂት
(ነገርግን የፖለቲካ ተፅዕኖ
የማሳደር አቅም ያላቸው)የማህበረሰቡ ክፍሎችን ተጠቃሚ ቢያደርግም መላውን ማህበረሰብ ግን ያዳክማል፡፡
‹‹ዘ ሎው››ን ሳነብ ባስቲያት
ከዘመናችንም ሆነ ከየትኛውም ዘመን ብዙም ልዩነት የሌለውን የእሱን ዘመን መንግስታዊያን(statists) የገለፀበት ፍፁም ትክክል
አቀራረብ አስደናቂ ነው፡፡ የባስቲያ ዘመንን የፈረንሳይ ‹‹ሶሻሊስቶች›› እርዳታ፣ ትምህርት እና ምግባርን አዋህዶ እንደ አንድ
የሚያቀርብ የተዛባ ቀኖና ነበራቸው፡፡ እውነተኛ እርዳታ በግብር በሚፈፀም ዝርፊያ አይጀምርም የሚል ነጥብ አስጨብጧል፡፡ የመንግስት
ትምህርት አሰጣጥ እውነተኛ ትምህርት ሳይሆን መንግስታዊ፣
አመለካከትን የማስቀየር (brainwashing) ሥራ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ በተጨማሪም አንድ ትልቅ ወሮበላ (መንግስት) ከአንድ
የህዝቡ ክፍል (በህጋዊ) የዘረፈውን አብዛኛውን ለራሱ አስቀርቶ ጥቂቱን ለተለያዩ ‹‹ችግረኛ›› ግለሰቦች ማካፈሉ ‹‹ምግባራዊ››
ሊሆን አይችልም፡፡
ባስቲያት ወደፊት የሚነሱ የዓለማችን
ሁሉን አድራጊ እና አንባገነን መሪዎች አለምን በራሳቸው መልክ (መልካቸው ኮሚኒዝም ፣ ፋሽዝም፣ ‹‹ክብራማው ህብረት››
(glorious union)፣ ወይም ‹‹አለምአቀፍ ዲሞክራሲ››(global democracy) ይሁን) መልሰው ለመስራት የሚሹ መሆናቸውን
አስቀድሞ በመተንበይ፣ ሶሻሊስቶች ‹‹የአምላክን ቦታ መጫወት›› የሚፈልጉ
መሆናቸውን አስገንዝቧል፡፡ ሌላው ባስቲያት ያስተዋለው ሶሻሊስቶች በግዳጅ ማመሳሰልን፣ ሰርፀው ገብተው በሚንሰራፉ ደንቦች ህዝቡን
በግትር ስርዓት ማደራጀት፣ በጉልበት የሃብት እኩልነትን ማምጣትን እና አምባገነንነትን መፈለጋቸውን ነው፡፡ እነዚህ ደግሞ የነፃነት
ምግባራዊ ጠላት ናቸው፡፡
‹‹አንባገነናዊነት›› የግድ አንድ
የሚታይ አንባገነን ሊኖረው አያስፈልገውም፡፡ እንደ ባስቲያት ገለፃ የግድ የሚስፈልገው በፓርላማ ወይም በኮንግረስ የታወጀ ተመሳሳይ
ውጤት ማለትም በግዳጅ ማመሳሰልን የሚያመጣ ‹‹ህግ›› ነው፡፡
ባስቲያት አለማችን እጅግ በጣም
ብዙ ‹‹ታላቅ ሰዎች››፣ ‹‹የሃገራቸው አባቶች›› ያሏት ሲሆን በእውነታው ግን በአብዛኛው እነዚህ ሰዎች በሌሎች ላይ የመግዛት
ህመምተኛ ውስጣዊ ግፊት ያለባቸው አነስተኛ ጨቋኝ ገዢ(tyrant) ናቸው፡፡ የነፃ ማህበረሰብ ተሟጋቾች ለሁሉም ይህን መሰል ሰዎች
ጤናማ ንቀት ሊኖራቸው ያስፈልጋል፡፡
ባስቲያት አሜሪካን ያደንቅ ነበር፡፡
የ1850ዋ (ኢ.እ.ኤ) አሜሪካ የግለስብ የህይወት፣ ነፃነት እና ንብረት መብትን የሚጠብቅ፣ ለእሱ የመንግስት አምሳል በአለም ላይ ካሉ ሁሉ የቀረበ ማህበረሰብ መሆኑን አመልክቷል፡፡
ነገር ግን ለዚህ አመለካከቱ ሁለት ዋና ልዩ ሁኔታዎች አሉ፤ መንታዎቹ ክፉው ባርነት እና ክላሎታዊ ታሪፍ
(protectionist tariff)::
ፍሬደሪክ ባስቲያት በ1850(ኢ.እ.ኤ)
የገና ዋዜማ የሞተ ሲሆን የሚያደንቃት አሜሪካ በቀጣዮቹ አስራ አምስት ዓመታት (ከዛም በኋላ) ያለፈችበትን ብጥብጥ ለመታዘብ በህይወት አልቆየም፡፡ የዩኤስ
መንግስት በ1861 (ኢ.እ.ኤ) የደቡብ ግዛቶችን የወረረችበትን ወታደራዊ ዘመቻን፣ የ300,000 ዜጎችን ግድያ፣ እና የክልሎቹን
ከተሞች፣ እርሻዎች እና ንግዶችን የቦንብ ድብደባ፣ ቃጠሎ እና ብዝበዛን፤ በነፃነት አዋጁ ላይ ቃል ከተገባው የዜጎችን ህይወትን፣
ነፃነትን እና ንብረትን የመጠበቅ ቃል ጋር በየትኛውም መንገድ የሚጣጣም እንደሆነ አይቆጥረውም ነበር፡፡ በህይወት ቆይቶ ተመልክቶ
ቢሆን ኑሮ ‹‹ህጋዊ ግድያን›› (legal murder) በ ህጋዊ ብዝበዛ (legal plunder) ላይ ከሁለቱ ታላቅ የመንግስት
ሃጢያቶች አንዱ ብሎ ይጨምረው ነበር፡፡ በአማካኝ 50 በመቶ የታሪፍ መጠን፣ ግዙፍ የተባበረ የነፃ ማህበራዊ አገልግሎት ዘዴውን
እና ለ25 ዓመታት የቆየ መከላከያ የሌላቸውን ህንዳውያን ላይ የፈፀመውን ዘር ማጥፋት ቢመለከት ድህረ ጦርነት ሪፓብሊካን ፓርቲን
የአሜሪካ መርህ ከሃዲ እና አንደኛ ደረጃ በዝባዦ አድርጎ ይመለከተው ነበር፡፡
ባስቲያት በ‹‹ ዘ ሎው›› የመጨረሻ ገፆች አካባቢ የነፃ ማህበረሰብ (ከሶሻሊዝም
በተቃራኒ) ስምምነትን (harmony) (እጥረትም ቢሆን) የሚያብራራ ‹‹የኢኮኖሚ ሳይንስ›› አስፈላጊ መሆኑን ብልህ ምክሩን ሰጥቷል፡፡
ይህንን ግብ ለመምታትም እሱ ራሱ የኦስትሪያ የሥነ ኢኮኖሚ ትምህርት ቤት (Austrian school of economics) ዘመናዊ
ፅሁፎች መንገድ ከፋች የሆነ ‹‹ኢኮኖሚክ ሃርመኒስ›› የተሰኘ
መፅሃፍ አሳትሟል፡፡ በእኛ ዘመንም ሆነ በባስቲያት ዘመን ወረርሽኝ የሆነውን አውዳሚው የሶሻሊስት ስርዓትን ለመዋጋት፣ የገበያ ስርዓትን (እና የፖለቲካውን እውነታ) በሚገባ ለመረዳት ምትክ የሌለው ስራ ነው፡፡ ይህንን መጣጥፍ ከሌሎች የሄነሪ ሃዘሊትን
ኢኮኖሚክስ ኢን ዋን ሌሰን እና መራይ ሮትባርትን
ፓወር ኤንድ ማርኬት ከመሳሰሉ ዘመን አይሽሬ የነፃ ገበያ አቀንቃኝ
ፅሁፎችን ጋር ያነበበ የዘመናችንንም ሆነ የየትኛውንም ዘመን የሶሻሊስት ቅዠቶች ማጋለጥ የሚያስችል በቂ አእምሯዊ ብቃት ይኖረዋል፡፡
ሜሪ ላንድ የሚገኘው ሎዮላ ኮሌጅ የስነ ኢኮኖሚ ፕሮፌሰር እና የሚሰስ ኢንስቲትዩት ሲንየር መምህራን አንዱ የሆኑት ቶማስ ዲሎሬንዞ ይህን መንደርደሪያ የፃፉት 2007 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) ነው፡፡ ዘ ሎውን እንድናነበው ጥሩ ጉጉት የፈጠሩብን ይመስለኛል፤ መጣጥፍን በተከታታይ አስነብባለሁ፡፡ ቸር ያቆየን፡፡
Ludwig von Mises Institute, CC BY 3.0 <https://creativecommons.org/licenses/by/3.0>, via Wikimedia Commons
https://commons.wikimedia.org/wiki/File:PortraitBastiat.jpg
Comments
Post a Comment