ረሃብ ክፉ ነው፡፡ ረሃብ አንጀትን ብቻ አይደለም የሚያጥፈው፡፡ አንገትን
ያሳጥፋል፣ አስደፍቶ፡፡ ወዝን ያጠፋል፡፡ ግርማ ሞገስን ይነጥቃል፡፡ ረሃብ ክፉ ነው፡፡ ሰውየው የዚሁ የክፉው ረሃብ ምርኮኛ፣ የረሃብ
ሰንሰለት እስረኛ ናቸው፡፡ ረሃብ አንጀታቸውን ብቻ አይደለም ያጠፉት አንገታቸውን ጭምር እንጂ፡፡ ግርማ ሞገሳቸውን ነጥቆ፣ ወዛቸውን
መጦ ‹‹ረሃብተኛ›› አርጓቸዋል፡፡ ታዲያ ሌላ ምን ይባላላል፤ ረሃብ ስማቸውን ቀምቶ ‹‹ረሃብተኛ››፣ ‹‹ችግረኛ›› ወይም ፈረንጆቹ
እንደሚሉት ‹ሆምለስ› (homeless) የተሰኙ አዳዲስ ስሞች አሰጣቸው፡፡
ይህ ሰው ኑሮ የተጫናቸውን፣ የሚቀምሱት ያጡትን ሁሉ ለማመልከት የተፈጠረ
ተምሳሌታዊ ሰው አይደለም፡፡ አቶ ኦስትሪያቮቭ ተብሎ የሚጠራ ዩክሬናዊ ደም ያለው ጣልያን ውስጥ የሚኖር ነዳይ ነው፡፡ ታሪኩን የዘገበው
ቢቢሲ ምን ያህል ቀናት ካለምግብ ያለፈቃዱ እንደፆመ ባይነግረንም መራብ ግን ተርቧል፡፡ እናም የታጠፈ አንጀቱን ለማላወስ ወደ አንዱ
ሱፐርማርኬት ገባ እና ዳቦ፣ ሁለት ፍሬ አይብ እና የታሸገ ስጎ አንስቶ ለዳቦው ብቻ ከፍሎ ሊወጣ ሲል ጉዳዩን ሲያስተውል የነበረ
ሌላ ተጠቃሚ ለጥበቃዎች አሰታውቆ አስያዘው፡፡ ሳይከፍል ይዞት ሊወጣ
የነበረው ቺዝ እና ስጎ 4.50 የሜሪካ ዶላር ዋጋ ያለው ነው፤ በኢትዮጵያ ገንዘብ ብር ማለት ነው፡፡ እናም በፖሊስ እጅ ወደቀ፤ በ2011 እንደ ምዕራባውያን
አቆጣጠር፡፡ በ2015 ዓ.ም (አሁንም በምዕራባውያን አቆጣጠር) ፍርድ ቤቱ (ለዚህች ጉዳይ እስከዛ የማንን ጎፈሬ ሲያበጥር እንደነበር
እንጃ) ጥፋተኛ ብሎ ስድስት ወር እስራት እና 100 ይሮ የገንዘብ ቅጣት ወሰነበት፡፡
ርቦት የሰረቀ የመጀመሪያው ሰው አይደለም፡፡ እግዲያውስ የሱን ጉዳይ ዜና
ያደረገው ምንድን ነው? ይህን ጉዳይ ዜና ያደረገው የሰውየው ስርቆት ወይም የፍርድ ቤቱ ቅጣት ሳይሆን ጉዳዩ የቀረበለት የጣሊያን
ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት የሰጠው ውሳኔ ነው፡፡ (ይህ ችሎት የህግ ጉዳይን ብቻ የሚመለከት ችሎት ነው፤ ፍሬ ነገርን በተመለከተ
አይመለከተውም፡፡) ሰውየው ሲያዝ ገና ከሱቁ ክልል አልወጣም እና ወንጀሉ
ከስርቆት ወደ ስርቆት ሙከራ ተቀይሮ ቅጣቱ እንዲቀልለት ነበር፡፡ የሰበር ችሎቱ ግን ያልተጠበቀ ውሳኔ ሰጠ፤ እንደሚከተለው፡-
“The condition of the defendant and the circumstance in which the seizure of
merchandize took place prove that he took possession of that small amount of
food in the face of an immediate and essential need for nourishment, acting
therefore in the state of necessity.” ‹‹ተከሳሹ ያለበት ሁኔታ እና ሸቀጦቹን በእጅ ያደረገበት አካባቢያዊ
ሁኔታ አነስተኛ መጠን ያለውን ምግብ የወሰደው አጣዳፊ እና አንገብጋቢ
ራስንን የመመገብ አስፈላጊነት ውስጥ በመሆኑ አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ የፈፀመው ነው፡፡›› እግዲያስ? እንግዲያማ፣ ወንጀል አልተፈፀመም
ብሎ ሰውየውን በነፃ አሰናበተው፡፡
ይህ ውሳኔ ነው ፍርድ ቤቱ መሰረት ስላደረገው መርህ እንድፅፍ፣ ጥያቄ
እንዳነሳ ብሎም የአገራችን ህግ ምን እንደሆነ (is) ምንስ መሆን እንዳለበት (ought to) እንድፈትን ያነሳሳኝ፡፡ በወንጀል
ህግ ወንጀል ቢፈፀምም ፈፃሚውን ድርጊቱን ህጋዊ የሚያደርጉ፣ ይቅርታ የሚያሰጡ እና የማያስቀጡ እንዲሆኑ የሚያደርጉ የሞያ ስራ ግዴታ፣
የተበዳይ ፈቃድ፣ ራስን መከላከል የመሳሰሉ መርሆች አሉ፡፡ እነሱም በወንጀል ህግ ውስጥ ተቀባነት ካገኙ ቆይቷል፡፡ የ16ተኛው ክ/ዘመን
አውሮፓዊ ዳኛ ፍርድ ሲሰጡ ያቀረቡት መከራከሪያ ለዚህ ምስክር ሆነናል፡፡ ከ16ኛው ክ/ዘመን በፊት ምሳሌ ቢፈለግ ባይታጣም፡፡
“ in every law there are some things which when they happen a man may break the
word of the law, and yet not break the law itself; and such things are exempted
out of the penalty of the law … where the words of them are broken to avoid
greater inconveniences, or through necessity, or by compulsion ….” በእያንዳንዱ ህግ ውስጥ በሚፈጠሩበት ጊዜ ሰው ህጉን ራሱን ሳይጥስ የህጉን
ፊደላት ግን የሚጥስባቸው ነገሮች አሉ፤ እነዚህ ነገሮች ደግሞ የህግ ቅጣት
አያገኛቸውም … ይህ የሚሆነው ግን የህጉ ፊደል የተጣሰው የበለጠ ጉዳትን፣ ወይም በአስፈላጊ ሁኔታ፣ ወይም በመገደድ
ለማስወገድ ሲሆን ነው፡፡
የጣልያኑ ሰበር የተጠቀመበት የአስገዳጅ ሁኔታ መርህ ከእነሱ ረድፍ የሚመደብ
ነው፡፡ የአስገዳጅ ሁኔታ(Necessity) መርህ አስፈላጊ አድራጎት፣ duress of circumstance፣ duress by
necessity or coercion ተብሎም ይጠራል፡፡ ይህን መርህ በተመለከተ ሊፀፍ የተነሳ ሁሉ ሳይጠቅሰው ሊያልፍ የማይችል ጉዳይ
አለ፡፡ በህግ ትምህርት ቤቶች እና በወንጀል ህግ ማብራሪያ መፅሃፍት አስገዳጅ ሁኔታን በተነለከተ ሲነሳ ሳይነሳ ሊቀር የማችል ጉዳይ
ነው፡፡ ‹አስገዳጅ ሁኔታ›ን በተለያየ አቅጣጫ እና መጠን (extreme) መፈተን እንዲቻለን ጠቃሚ አስተዋፆ አለውና ላካፍላችሁ፡፡
ታሪኩ እውነት ነው፤ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1880ዎቹ የተፈፀመ፡፡
ቶም ደድሊ፣ ኤድዋርድ ስቴፈንስ፣ ኤድሞንድ ብሩክስ እና ሪቻርድ ፓርከር በደቡብ አትላንቲክ ከምርድ 700 ማይል ርቀው ሚግኖኔት
በተባለች የሽርሽር ጀልባ ሲቀዝፉ ከባድ ወጀብ ገጠማቸው፡፡ መዓበሉ ጀልባዋን ደህና አድርጎ ጎድቷት ስለነበር አራቱ ሰዎች ክፍት
ወደ ሆነች አነስተኛ ጀልባ ለመሸሽ ተገደዱ፡፡ ከሁለት ጣሳ ቀይ ስር በስተቀር ምንም ምግብም ሆነ ውሃ አልነበራቸውም፡፡ በአራተኛው
ቀን አንድ አነስተኛ ኤሊ ያዙ እና እስከ አስራ ሁለተኛው ቀን ባለው ጊዜ ሙጥጥ አድርገው ጨረሷት፡፡ ፓርከር የሌሎችን ምክር አልሰማ
ብሎ የባህሩን ውሃ ጠጣ እና ታመመ፡፡ የውቂያኖስ ውሃ የጠጣ ሰው መቼስ ጨው በጥብጦ ጠጣ እንጂ ውሃ ጠጣ አይባል፡፡
ለሃያ ቀናት የተመገቡት ቀይስር እና ያችን ኤሊ ብቻ ነበር፡፡ ረሃብ አቅላቸውን
ያሳታቸው ስቴፈን እና ደድሊ ብሩክስ በሃሳባቸው ባይስማማም የባህር ጉዞው የመጀመሪያው የሆነውን የ17 ዓመቱን ፓርከርን ገድለው ለመመገብ
ወሰኑ፡፡ ይህ እናት አባት የሌለው ወጣት በወቅቱ ከሁሉም የደካከመው
እሱ ነው፡፡ ስቴፈን እና ደድሊ እኛ አገራችን እንግሊዝ ቤተሰቦቻቸን
የሚጠብቁን ቤተሰብ አስተዳዳሪዎች ፓርከር ግን ቤተሰብም የሌለው አሁንም ደካክሞ ለሞት የተቃረበ ነው ብለው ለውሳኔያቸው ምክንያት
ሰጡ፡፡ ፓርከር እንዲገድሉት ፈቃዱን አልስጠም ሆኖም ግን ለመቃወምም አቅም አልነበረውም፡፡ ደድሌ ፊቱን ለሰማያት ሰጥቶ ይቅርታውን
ፈጣሪ እንዲለግሰው ተማፅኖ - በፀሎት - ቢላውን አውጥቶ የፓርከርን ህይወት
ቀጠፈ፡፡ ቀሪዎቹ ስቴፈን፣ ደድሊ እና የምግብ ጉዳይ ሲን ጀርባውን ሊሰጥ ያልቻለው ብሩክስ ለቀጣዮቹ የጉዞ ባልደረባቸውን
ስጋ ተመገቡ ደሙን ጠጡ፡፡ የሆሊሁድ ሆረር ፊልም አይደለም የምታነቡት፤ ድጋሚ ላስታውሳችሁ፣ እውነተኛ ታሪክ ነው፡፡ በአራተኛው
ቀን ምንም እንኳ በመልካም ጤንነት ሆነው ባይሆንም ‹ነፍስ አድንኖች› ደርሰው አተረፏቸው፡፡ የፓርከርን ስጋ ባይመገቡ ኑሮ በረሃብ መሞታቸው ኤቀሬ ነበር፤ ፓርከርም ቢሆን ከእነሱ ይበልጠ ተጎድቶ ስለነበር
ቀድሟቸው ነበር የሚሞተው፡፡
ከባህር ወደ ምድር ከተመለሱ በኋላ ግን ስቴፈንሰ እና ደድሊ ከመታሰር
እና ለፍርድ ከመቅረብ አልተረፉም፡፡ ጉዳያቸው የቀረበለት ፍርድ ቤት ተከሳሾቹ በወከሏቸው የህግ ባለሞያዎች አማካኝነት አስገዳጅ
ሁኔታ ውስጥ ነበረን ብለው ቢከራከሩም፤ ፍርድ ቤቱም እማኝ ዳኞች እንዳረጋገጡት በአስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ መሆኑን ባይክድም
በአስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸው ግን የፈፀሙትን ግድያ ህጋዊ ወይም ይቅርታ የሚያሰጥ አሊያም የማያስቀጣ አያደርገውም በሚል ጥፋተኛ
ብሎ በሞት እንዲቀጡ ወስኗል፤ በእርግጥ በኋላ ላይ ቅጣቱ ወደ ስድስት ወር ቢወርድላቸውም፡፡ ጉዳዩን ካዩት አምስት ዳኞች መካከል
ፍርዱን ይፋ ያደረጉት (ምናልባትም የፃፉት) ዳኛ ሎርድ ኮልሪጅ ለውሳኔያቸው ሁለት ምክንያቶች አትተው ነበር፡፡
የመጀመሪያው ምክንያት ስነምግባራዊ(morality) ነው:: ክርክራቸው
ከስነምግባር አንፃር ትክክለኛው አካሄድ ለሌሎች ራስን መስዋዕት ከማድረግ ውጪ ሌላ ሊሆን አይገባም ነበር የሚል ነው፡፡ ሌሎቹ በህይወት እንዲኖሩ ራስን መሰዋት ነው አግባብ
የሆነው አካሄድ የሚል ነው መከራከሪያው፡፡ እዚህ ጋር ግን በውስጤ
የሚነሳ ጥያቄ አለኝ፤ ፓርከር በቃ እኔን ግደሉኝ እና ተመገቡኝ ቢል ኖሮ እነዚህ ሰዎች ወንጀል አልፈፀሙም ወይም ሊቀጡ አይገባም
ብለው ይወስኑ ነበር? ለነገሩ ዳኛው ራሳቸው ያመኗት ሃቅ አለች፡፡ እንዲህ አሉ፡- “we are often compelled to
set up standards we cannot reach ourselves, and to lay down rules we could not
ourselves satisfy.” ‹‹ብዙ ጊዜ ራሳችን የማንደርስባበውን መስፈርቶች፣ ራሳችን የማናከብራቸው ህጎች ለማውጣት እንገደዳለን››
ሁለተኛው ምክንያትስ? መልሱ፡- “…the difficulty of measuring necessity and
selecting the victim … by what measure is the comparative value of lives to be
measured?” ‹‹ … አስገዳጅ ሁኔታን ለመመዘን እና ተበደዩን ለመምረጥ አስቸጋሪ መሆኑ … የህይወቶች ተነፃፃሪ ዋጋ የሚለካው
በምን ሚዛን ነው?›› ዳኞቹ ችግራቸው አስገዳጅ ሁኔታን ለመለየት መስፈርቱ ምን መሆኑን እና በተለይ ህይወትን ከህይወት አስበልጦ
ፓርከርን ለመግደል ሚዛን ማግኘት ነው፡፡ አሁንም ግን ጥያቄ አለኝ አንድን ነገር ለማድረግ አስቸጋሪ መሆኑ በራሱ ብቻ ስህተት ያደርገዋል?
ይሁንላቸውና የመመዘኛ መስፈርት እንፍጠርላቸው እና ፓርከርን የገደሉት ማን እንደሚገደል እጣ ተጣጥለው እጣው ፓርከር ላይ ወድቆ
ቢሆን ኑሮስ ወንጀል መች ተፈፀመ ብለው ተከሳሾችን ነፃ ያደርጉ ነበር?
ከአውሮፓ እንውጣ እና የአፍሪካ ቀንድ፣ ኢትዮጵያ እንምጣ፡፡ ሦስት ጥያዎች ይነሳሉ፡፡ የኢትዮጵያ ህግ የአስገዳች ሁኔታ የወንጀል መከላከያን
ያውቀዋል? ህጉ ምን ይላል ወይም ከላይ ያሉት ጉዳዮች ቢቀርቡለትስ ህጋችን ምን ይፈርዳል?(is?) ህጉስ ተገቢ (መሆን የሚገባው)ነው?(ought
to?)
የመጀመሪያው ጥያቄ፣ የኢትዮጵያ ህግ የአስገዳጅ ሁኔታ የወንጀል መከላከያን ያውቀዋል? በሚገባ፡፡ ድንጋጌው የሚከተለው ነው፡፡
አንቀፅ 75 አስገዳጅ ሁኔታ
የራስን ወይም
የሌላ ሰውን መብት በቅርብ ከሚደርስ ከባድ አደጋ ለማዳን የተፈፀመ
ድርጊት፣ አደጋውን በሌላ መንገድ ማስወገድ
የማይቻል ከሆነና አድራጊው ከሁኔታው ጋር ተመጣጣኝ የሆኑ ዘዴዎችን የተጠቀመ ከሆነ አያስቀጣም፡፡
የሰው ህይወት
ወይም ደህንነት የመጠበቅ ልዩ የሙያ ግዴታ ያለበት ሰው የሚፈፅመው ተመሳሳይ ድርጊት በዚህ አንቀፅ ስር ከቅጣት አያድንም፤ ቢሆንም
ፍርድ ቤቱ በመሰለው ቅጣቱን ያቃልልለታል፡፡
አንቀፅ 76 የአስገዳጅ ሁኔታን ወሰን መተላለፍ
በነገሮች አካባቢ ሁኔታዎች መሰረት
በአደጋ ላይ የሚገኘውን መብት መስዋዕት ማድረግ ተገቢ ሆኖ የተገኘ እንደሆነ ወይም በሌላው ሰው መብት ላይ የተደረገው ጉዳት ካስፈላጊው
መጠን በላይ እንደሆነ፤ ወይም አድራጊው የተገኘበት አስገዳጅ ሁኔታ ወይም የአደጋ ሁኔታ በራሱ ጥፋት የመጣ እንደሆነ ፍርድ ቤቱ
እንደመሰለው ቅጣቱን ያቀልለታል፡፡
ሁለተኛው ጥያቄ፣ ህጉ ምን ይላል ወይም ከላይ ያየናቸውን
የመሰሉ ታሪኮች ቢቀርቡለት ምን ይመልሳል?
በኢትዮጵያ የወንጀል ህግ አንድ ድርጊት በአስገዳጅ ሁኔታነት እንዲመደብ ማሟላት የሚገባው መስፈርቶች አሉ፡፡
(1) አንድን መብት ለመጠበቅ በሌላ መብት
ላይ የተፈፀመ፣ (2) በቅርብ ከሚደርስ ከባድ አደጋ ለመታደግ፣ (3) የመጨረሻ አማራጭ ሆኖ፣ (4) ተመጣጣኝ ዘዴ በመጠቀም
የተፈፀመ መሆን ይገባዋል፡፡ ቀጥለን ከላይ የተመለከትናቸውን ጉዳዮች በነዚህ መስፈርቶች በመመልከት በእርግጥ ህጉ ምን እንደሆነ
እንመልከት፡፡
የጣሊያኑን ነዳይ በዚህ ህግ ፊት አቁመን ድርጊቱን እንመርምር፡-
1.
የተራበው
ሰው በህይወት የመኖር መብት አለው፣ ካልበላ ደግሞ በህይወት መኖር አይችልም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የሱርማርኬቱ ባለቤት የንብረት
መብት አለው፣ ንብረቱ ከስርቆት ካልተጠበቀለት መብቱ ተገፋ ማለት ነው፡፡ ድርጊቱ ለመኖር በንብረት ላይ የተፈፀመ ነው፡፡
2.
በቅረብ
የሚደርስ ከባድ አደጋ ( imminent and serious danger) የነበረ መሆኑ በሰውየው የረሃብ ደረጃ ይወሰናል፡፡ ዜናውን
በመገናኛ ብዙሃን ከማንበብ ውጭ ይህ ሰው ለምን ያህል ጊዜ በምን ያህል መጠን እንደተራበ ለማወቅ ሙለውን ውሳኔ ማንበብ እና መለየት
አልቻልኩም፡፡ ሆኖም ግን ቢቢሲ ከፍርድ ውሳኔው ላይ ከፈርድ ቤቱ ውሳኔ ላይ ጠቅሰው ያሰፈሩት አንቀፅ ላይ ሰውየው አጣዳፊ እና
አስፈላጊ (immediate
and essential) ፍላጎት እንደነበረው
ስለተጠቀሰ ምግብ ማጣቱ በቅርብ የሚደርስ ከባድ አደጋ ደቅኖበታል ለማለት ያስችለናል፡፡
3.
ስርቆት
የመጨረሻ አማራጭስ ነበር? ከመስረቅ በፊት መለመን ሌላ አማራጭ ነው፡፡ በእኛ አገር ሁኔታ ፣ በእኛ ሃገር ሁኔታ የሚለውን ልተወውና
አዲስ አበባ (ከአዲስ አበባ ውጪ ያደረግሁት ጉዞ ውስንንነት ያለኝን እውቀት ውስን ስለሚያደርገው) ውስጥ ለምኖ መብላት የሚባል አማራጭ አለ፡፡ የጣሊያኑ ሰውየ ይህን አማራጭ
ሞክሮ የነበረ ይሁን አይሁን አላቅም፡፡ አዲስ አበባዊ ቢሆን ኖሮ ግን ይህ ምርጫ ነበረው፡፡
4.
አራተኛው
ተመጣጣኝነት ነው፡፡ ድርጊቱ የተፈፀመበት መንገድ የድርጊቱን አላማ ለማስፈፀም የሚያስፈልገውን ያህል ብቻ መሆን አለበት፡፡ ለምሳሌ
እያወያየን ያለው ሰውየ ለመስረቀ እንዲችል ሰራተኞችን ቢያግት ወይም ቢደበድብ ተመጣጣኝ ድርጊት ነው ሊባል አይችልም፤ ወደ ውስጥ
ያለችግር ገብቶ የሚፈልገውን አንስቶ መውጣት ይችላልና፡፡ ያደረገውም ይህንኑ ስለሆነ ድርጊቱ ተመጣጣኝ ነው ማለት ይቻላል፡፡
የጣሊያኑ ሰውየ በኢትዮጵያ ህግ ቢዳኙ ይቀጣሉ፤ የኢትዮያጵያ ህግ የአስገዳጅ ሁኔታ መስፈርቶች መካከል ‹‹በሌላ መንገድ
ማስወገድ የማይቻል›› ሲሆን ወይም የመጨረሻ አማራጭ ሲሆን መሆን የሚገባው ቢሆንም የመለመን ሌላ አማራጭ መኖሩ የተራቡት ሰውዬ
ስርቆት በአስገዳጅ ሁኔታ የተደረገ የማያስቀጣ ወይም ይቅርታ የሚያሰጥ ድርጊት ሳይሆን ወንጀል ነው፡፡
የእንግሊዛውያኑን መርከበኞች ጉዳይ ደግሞ እንመርምር፡-
1.
በዚህ
ጉዳይም ሁለት ተፃራሪ መብቶች አሉ፤ የተበይው የመኖር መብት እና የበይዎች የመኖር መብት፡፡
2.
ለበርካታ
ቀናት ያለምግብ የቆዩ በመሆኑ ህይወታቸው አደጋ ላይ ነው፤ በአጭሩ በወቅቱ እየሞቱ ነበር፡፡ ስለሆነም ድርጊታቸው ‹‹በቅርብ ከሚደርስ
ከባድ አደጋ›› ለመዳን የተፈፀመ ነው፡፡
3.
ግድያውስ
የመጨረሻ አማራጭ ነበር? ለዚህ ጥያቄ መልስ የምናገኘው ምግብ የሚያገኙበት ሌላ መንገድስ ነበር? ለሚለው ጥያቄ የምንሰጠው መልስ
ለዚህም ጥያቄ መልስ ነው? ከታሪኩ ልንረዳ እንደምንችለው በወቅቱ ማንም ሊያስበው የሚችል ምግብ የሚገኝበት ሌላ አማራጭ የለም፡፡
4.
ቀጥሎ
የተመጣጣኝነት ጥያቄ ይነሳል፡፡ ፓርከርን ለመመገብ የግድ መገደል ይኖርበታል፣ ለመግደል ደግሞ በእጃቸው የሚገኘውን መሳሪያ ተጠቅመዋል፡፡
ግድያው የተፈፀመበት መንገድ ተመጣጣኝ አይደለም ለማለት የሚያስችል ምንም ምክንያት የለም፡፡
ስለዚህ የእንግሊዛውያኑን የደድሊን እና የስቴፈንን ጉዳይ በኢትዮጵያ የወንጀል ህግ ስንዳኘው የምናገኘው ውጤት በህጉ
አንቀፅ 75 ስር ያሉ መስፈርቶችን ስለሚያሟላ ፓርከርን ገድለው መመገባቸው በአስገዳጅ ሁኔታ የተደረገ ስለሆነ ድርጊታቸው የማያስቀጣ
ወይም ይቅርታ የሚያሰጥ ድርጊት ስለሆኑ በነፃ መሰናበት ይሆን ነበር፡፡ ታዲያ ህጋችን ኢ-ሰብዓዊ አልሆነም?!
ሦስተኛው ጥያቄ፣ ህጉስ ተገቢ (መሆን የሚገባው)ነው?(ought
to?)
የአስገዳጅ ሁኔታ የወንጀል ክስ
መከላከያ ጭራሽ አያስፈልግም የሚል አቋም የለኝም ፡፡ የአስገዳጅ ሁኔታ ህግ ከሌለ በነበልባል እሳት ውስጥ ታፍኖ በሞት እና በህይወት
መካከል ያለ ሰውን ለመርዳት ሲበር ከፊቱ የተደነቀረውን ቀይ መብራት የጣሰውን የእሳት አደጋ መኪና አሽከርካሪን ልነቀጣነው፤ ቦታው
ላይ ደርስውስ ወደ ውስጥ አላስገባ ያላቸውን በር ሰብረው የገቡ የእሳት አደጋ ሰራተኞችን በንብረት ላይ ጉዳት በማድረስ ወንጀል
ወንጀለኛ ልንላቸው ነው፤ በሞት አፋፍ ላይ ያለን በሽተኛ ጭኖ የሚበር አምቡላንስ መንገድ ስለተዘጋጋበት በተቃራኒው አቅጣጫ ቢጓዝ
ልንቀጣው ነው? ሌላም ሌላም፡፡ ጥያቄ የማነሳው ሁለት ነጥቦች ላይ ነው፡፡
ህጉ ‹‹የራስን ወይም የሌላ ሰውን
መብት በቅርብ ከሚደርስ ከባድ አደጋ ለመጠበቅ›› ይላል፡፡ ስለዚህ የራሳችንን ወይም የሌላን ሰው የንብረት መብት ከሚደርስበት አደጋ
ለማትረፍ የሰው ህይወት ማጥፋት ህጋዊ ነው ማለት ነው? ፍፁም ሊሆን አይችልም፡፡ የወንጀል ህጉ ድንጋጌ ግን ይህን ነጥብ በግልፅ
ባለመጥቀሱ ክፍት ፈጥሯል፡፡ ለራሱ አነስተኛ መብቶች የሌላውን ከፍተኛ መብቶችን ለመሰዋት ለሚዳዳው ሰው ይሁንታ እየሰጠ ነው፤ በዝምታው፡፡
በአንድ እጁ አንድ ጥንታዊ፣ የብራና፣ ብቸኛ ቅጂ የሆነ ሰነድ በአንድ እጁ እሳት ይዞ እናዳትጠጉኝ ካለበለዛ አቃጥለዋል እያለ እየዛተ
ያለ እና የእውነትም ሊያደርገው የሚችለውን ሰው ሰነዱን ለማትረፍ በጥይት ተኩሶ የገደለን ፖሊስ ነፃ ሊያደርግ ነው፡፡ ስለዚህ በህጉ ላይ በግልፅ ጥበቃ የሚደረግለት መብት ጥበቃ ከማይደረግለት መብት
የበለጠ መሆን አለበት፡፡ ልክ ከላይ እንደተመለከትናቸው የእሳት አደጋ
ሰራተኞች ማለት ነው፤ የመኖር መብትን ከጉዳት ለመጠበቅ የንብረት መብትን ጥሰዋል፡፡ የመኖር መብት፣ ህይወት ከንብረት መብት፣ ከቁሳቁስ
ስለሚበልጥ ተገቢ ድርጊት ነው፡፡ ስለሆነም በወንጀል አያስቀጣም፡፡ ስለዚህ ህግ አውጭው ድንጋጌውን ‹የራስን ወይም የሌላ ሰውን
የበለጠ መብት በቅርብ ከሚደርስ ከባድ አደጋ ለመጠበቅ› በሚል ሊያሻሽለው ይገባል፡፡ ማሻሻያ አቅርቦ እንዲሻሻል ማድረግ በዋነኝነት
ይህ ሃላፊነት የፍትህ ሚንስቴር (ከጥቂት ጊዜ በኋላ የጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ፅ/ቤት ) ነው፡፡ ይህ ነው የመጀመሪያው ድንጋጌው መሆን
ነበረበት የምለው፡፡
ሁለተኛው ነጥቤ የድንጋጌው (የአንቀፅ 75) ሁለተኛ ክፍል ነው፡፡ የአስገዳጅ
ሁኔታ መከላከያ ‹‹የሰው ህይወት ወይም ደህንነት የመጠበቅ ልዩ የሙያ ግዴታ ያለበት ሰው የሚፈፅመው [ከሆነ] ….. ከቅጣት አያድንም፤ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ በመሰለው ቅጣቱን ያቃልልለታል፡፡››
ይላል፡፡ እግዲያውስ በእሳት የተከበበውን ሰው ለማዳን በር ሰብሮ የገባውን የእሳት አደጋ ሰራተኛ የሰው ህይወት እና ደህንነት የመጠበቅ
ሞያዊ ግዴታ ስላለበት ብቻ ሊቀጣ ይገባል ማለት ነው? ድንጋጌው ማለት የፈለገው ይገባኛል፡፡ ማለት የፈለገውን ግን አላለም፡፡ ይህ
ደግሞ የአርቃቂው የትኩረት ችግር ነው፡፡ ድንጋጌው መፍትሄ ሊሰጥ የፈለገው በአሜሪካን አገር በነበረው ዩናይትድ እስቴት እና ሆልምስ
(United states v. Holmes) በተሰኘው ክርክር ምክንያት የነበረውን ድርጊት ነው፡፡ ለዚህ ክርክር መነሻው ባህር ላይ
ጭነት በዝቶባት ልትሰምጥ ከነበረችው መርከብ ራሱን እና የስራ ባልደረቦቹን ለማትረፍ ተሳፋሪዎቹን ወደ ባህር የዶለው ባህርተኛ በግድያ
ተከሶ ቀርቦ ነው፤ ፍርድ ቤቱ ይህ ባህርተኛ የተሳፋሪዎቹን ህይወት የመጠበቅ ሞያዊ ግዴታ እያለበት የፈፀመው ነው በሚል ቀጥተውታል፡፡
የወንጀል ህጉ(አንቀፅ 75) ድንጋጌ ሁለተኛ ክፍል እንደነዚህ ላሉ ጉዳዮች መፍትሄ ለመስጠት የታሰበ ቢሆንም አርቃቂው ዋጋ አሳጥቶታል፡፡
ሊሻሻል ይገባል፡፡
ሶስተኛው የኢትዮጵያ ወንጀል ህግ የአስገዳጅ ሁኔታ መከላከያ በጠቅላላው
የቀረበ መሆኑ ነው፡፡ ለዚህም ነው ከላይ የጠቀስኩት በእንግሊዝ ፍርድ ቤት የታየው በአስገዳጅ ሁኔታ ሰበብ አሰቃቂ ግድያ እና ሰው
ስጋ መብላት (cannibalism) እኛ ሃገር ቢፈፀም እና በኛ ህግ ቢዳኝ አስገዳጅ ሁኔታ ነው ተብሎ ወንጀል ፈፃሚዎቹ ነፃ የሚለቀቁት፡፡
ይህ እጅግ በጣም ኢ-ሰብዓዊ እና በየትኛውም የስነ-ምግባር ፍልስፍና ዘርፍ ተቀባይነት ሊያገኝ የማይገባ ነው፡፡ ሰው እኮ ነን፡፡
አሁንም እደግመዋለሁ ሰው እኮ ነን፡፡
የአስገዳጅ ሁኔታ ህግ መኖሩ አስፈላጊ መሆኑን ቀደም ሲል ገልጬዋለሁ፡፡
ነገር ግን ይህ ህግ የመግደል መብት ሊሰጥ አይገባም፤ ግድያ በልዩ ሁኔታ (exception) ከድንጋጌው ክልል ውጭ መደረግ ነበረበት፡፡
የእንግሊዙ የደድለ እና ስቴፈንስ ገዳይ ላይ የተሰጠው ውሳኔ ውስጥ ዳኛው የህይወትን ዋጋ አስመልክቶ እንዲህ ብለው ነበር፡- “Who is to be judge of this sort of
necessity? By what measure is the comparative value of lives to be measured? Is
it to be strength, or intellect, or what? It is plain that the principle leaves
to him who is to profit by it to determine the necessity to justify him in
deliberately take another’s life to save his own. In the present case the
weakest, the youngest, the most unresisting life was chosen. Was it more
necessary to kill him than one of the grown men? The answer is be, No.” ‹‹ የእንዲህ አይነቱ አስገዳጅ ሁኔታ ዳኛ የሚሆነው ማን ነው? የህይወቶች ተነፃፃሪ ዋጋ የሚለካው በምን ሚዛን ነው?
ጥንካሬ ነው፣ ወይስ የአእምሮ ብቃት ወይስ ምን? መርሁ ከድርጊቱ
ተጠቃሚ የሆነው ሰው ራሱ የራሱን ህይወት ለማዳን ሆን ብሎ የሌላውን ህይወት የመንጠቁን አስገዳጅ ሁኔታ ራሱ እንዲወስን እንደፈቀደለት
ግልፅ ነው፡፡ በያዝነው ጉዳይ ከሁሉም ደካማ የሆነው፣ ከሁሉም ልጅ የሆነው፣ ከሁሉም ይበልጥ ሊቃወም የማይችለው ህይወት ተመረጠ፡፡
ከትላልቆቹ አንዱ ሳይሆን እሱን መግደል ይበልጥ አስፈላጊ ነው? መልሱ አይደለም ነው፡፡ ›› ህይወትን ከህይወት አነፃፅሮ ማበላለጥ
የምንችልበት መስፈርት ሊገኝ ይችላል ወይ በሚል መንፈስ ነው ዳኞቹ ክርክር ያቀረቡት፡፡ ህይወት አንዱ ካንዱ ሊወዳደር የማይችል
በራሱ ምሉዕ፣ ሰውን ሰው ያደረገ የህላዊያችን ማዕከል ነው፡፡ ስለዚህ ዳኞቹ አመለካከታቸው ትክክል ቢሆንም የመስፈርት ማጣት ጉዳይ
ብቻ አድርገው ሊያቀርቡት ግን አይገባም፡፡
በአሰገዳጅ ሁኔታ ሰው መግደልን ከሚደግፉ መሃል የህግ ምሁሩ ረዳት ፕሮፌሰር
ፀሃ ወዳ ይገኙበታል፡፡ የወንጀል ህግ መሰረታዊ መርሆች በተባለው መፅሃፍ ይህን አትተዋል፡- ‹‹ … ብዙዎች የሚስማሙበት ሃሳብ
ከወንጀል ድርጊቱ ተነሳ የደረሰው ጉዳት ከአደጋው የተነሳ ሊደርስ ይችል ከነበረው ጉዳት ያነሰ እስከሆነ ድረስ ከድርጊቱ የተነሳ
የተፈፀመው ወንጀል የሰው መግደልም ሆነ ሌላ ቢሆን መከላከያው ተቀባይነት ሊያገኝ ይገባል የሚለው ነው፡፡ … ስለዚህ የአንድ ከተማ
ነዋሪዎች ህይወት ለማትረፍ የጥቂት ሰዎችን ህይወት መሰዋት አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ መከላከያው ተቀባይነት ሊያገኝ ይገባዋል፡፡››
እዚህ ላይ ፕሮፌሰሩ የሳቱት ነጥብ ህይወት በቁጥር የሚለካ ሸቀጥ አለመሆኑን ነው፡፡ ያቀረቡት ክርክር ንብረትን የተመለከተ ቢሆን
ያስኬድ ነበር፤ ንብረት በቁጥር ሊበላለጥ ይችላል፡፡
አንባቢ ፍፁም እንዳይዘነጋው የምፈልገው ነጥብ የአስገዳጅ ሁኔታ መከላከያ
ራስን ከመከላከል (self defense) ያለውን ልዩነት ነው፡፡ ራስን በመከላከል ላይ ያለ ሰው ጉዳት የሚያደርሰው ሊያጠቃው በመጣ
ሰው ላይ ነው፣ አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ነኝ የሚል ግን የሚገድለው ንፁህ ሰውን ነው፤ ንፁህ ህይወት፡፡ የወንጀል ህጋችንም በአስገዳጅ
ሁኔታ ሽፋን የንፁህ ሰው ህይወትን በመንጠቅ የሰው ልጅ ህላዌን ትርጉም አሳጥቶታል፡፡
እና ምን ይጠበስ?(አንድ ወዳጄ አንድን ፅሁፍ ካነበበ በኋላ የሚጠይቀው ጥያቄ ነው፡፡) የወንጀል
ህጉ ደንጋጌ ግድያን ለአስገዳጅ ሁኔታ መከላከያነት እንዳይውል በልዩ ሁኔታ ይለየው፤ ህግ አውጪው በዚህ መለኩ ህጉን ያሻሽል፡፡
picture credit
https://www.flickr.com/photos/nzdave/2465592295
Comments
Post a Comment