Skip to main content

አፈንጋጩ ህግ፡ የፍሬደሪክ ባስቲያት ዘ ሎው

 


ፍሬደሪክ ባስቲያት መጣጥፉን ሲጀምር ህግ አፈንግጧል ይለናል፡፡ የህግ ተገቢ ቦታው እና አገልግሎቱን ያብራርናል፡፡ ቀጥሎም አፈንግጦ የት እንደደረሰ ያትታል፡፡ በሌላ አባባል የህግ ማፈንገጥ ከየት ወደ የት? ለምንስ? ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ ይሰጠናል፡፡ መልካም ንባብ፡-

ህግ አፈንግጧል! የመንግስት የፖሊስ ኃይልም አብሮ አፈንግጧል! እያልኩ ያለሁት ህግ ተገቢ አላማውን ስቷል ብቻ አይደለም፤ ከዓላማው ፍፁም ተቃራኒ የሆነ ዓላማን እንዲከተል ተደርጓል ጭምር እንጂ! ህግ የሁሉም አይነት ስግብግብነት መሳሪያ ሆኗል! ወንጀልን መቆጣጠርን ትቶ ህግ እራሱ ሊቀጣቸው ይገቡ የነበሩ ጥፋቶች ወንጀለኛ ነው፡፡

ይህ እውነት ከሆነ፣ ከባድ እውነታ በመሆኑ  አቻዬ ዜጎችን ትኩረት ወደ እዚህ ጉዳይ እንድስብ ምግባር ግድ ይለኛል፡፡

ህይወት ከአምላክ የተሰጠ ስጦታ ነው

ከአምላክ ሁሉን ነገር አጠቃሎ የያዘ ስጦታ ተቀብለናል፡፡ ይህ ስጦታ ህይወት ነው - አካላዊ፣ አእምሯዊ እና ምግባራዊ ህይወት፡፡

ሆኖም ህይወት ብቻውን ሊኖር አይችልም፡፡ የህይወት ፈጣሪ እንድንጠብቀው፣ እንድናዳብረው እና እንድናፈፅመው(ፍፅምናን እንድናለብሰው) ኃላፊነት ሰጥቶናል፡፡ ኃላፊነታችንን እንድንወጣ ደግሞ የአስደናቂ ችሎታዎች ስብስብ አቅርቦልናል፡፡ እንዲሁም በተለያዩ አይነት የተፈጥሮ ሃብቶች መሃል አስቀምጦናል፡፡ ችሎታዎቻችንን በመጠቀም እነዚህን የተፈጥሮ ሃብቶች ወደ ምርት ቀይረን እንጠቀምባቸዋለን፡፡ ህይወት የታሰበላትን መንገድ እንድትጓዝ ይህ ሂደት አስፈላጊ ነው፡፡

ሰው ማለት ህይወት፣ ችሎታ እና ምርት፣ በሌላ አባባል ግለሰባዊነት፣ ነፃነት እና ንብረት ነው፡፡ ብልጣብልጥ የፖለቲካ መሪዎች ማታለያ ምንም ሆነ ምን ሶስቱ የአምላክ ስጦታዎች የትኛውንም ሰብዓዊ ህግ ይቀድማሉ፤ ደግሞም የበላይ ናቸው፡፡

ህይወት፣ ነፃነት እና ንብረት የሰው ልጅ ህግን ስለፈጠረ የተገኙ አይደሉም፡፡ እንደውም በተቃራኒው ህይወት፣ ነፃነት እና ንብረት ቀድመው መኖራቸው  ነው መጀመሪያውኑም የሰው ልጅ ህግ እንዲያወጣ ያደረገው፡፡

ህግ ምንድን ነው?

እንግዲያውስ ህግ ምንድን ነው? በጋራ የተደራጀ የግለሰብ መብት ህጋዊ መከላከያ ነው፡፡

እያንዳንዱ ሰው ከአምላክ የተሰጠ ስውነቱን (person)፣ ነፃነቱን እና ንብረቱን የመጠበቅ ተፈጥሯዊ መብት አለው፡፡እነዚህ ሶስቱ መሰረታዊ የህይወት መስፈርቶች ሲሆኑ የአንደኛው ጥበቃ ሙሉ ለሙሉ በሌሎቱ በሁለቱ መጠበቅ ላይ የተመካ ነው፡፡ ችሎታዎቻችን ግለሰባዊነታችንን ለማስቀጠል ካልዋሉ ለምን ይውላሉ? ንብረትስ የችሎታዎቻችን ቅጣይ ካልሆነ ምንድን ነው?

እያንዳንዱ ግለሰብ ኃይልን ተጠቅሞ ጭምር ሰውነቱን፣ ነፃነቱን እና ንብረቱን የመጠበቅ መብት ካለው፣ እነዚህን መብቶች ወጥነት ባለው መንገድ ለመጠበቅ የሰዎች ቡድን የጋራ ኃይል ለመፍጠር የመደራጀት እና የመረዳዳት መብት ይኖረዋል፡፡ ስለዚህ የወል መብቶች መርህ የመፈጠሩ ምክንያትም ሆነ ህጋዊ መሰረት የሚያገኘው በግለሰብ መብቶች ላይ በመመስረት ነው፡፡ እናም የወል መብቶችን የሚጠብቀው የጋራ ኃይል በምትክነት ከተፈጠረለት ዓላማ ወይም ግብ ውጭ ሌላ ዓላማ እና ግብ ሊኖረው የሚችልበት ምክኒያታዊነት የለም፡፡ ስለሆነም አንድ ግለሰብ በሌላ ሰው ሰውነት፣ ነፃነት እና ንብረት ላይ ህጋዊ በሆነ መንገድ ኃይል ሊጠቀም እንደማይችለው ሁሉ የትኛውም የጋራ ኃይልም በተመሳሳይ ምክንያት የሌላውን ግለሰብ ወይም ቡድን ሰውነት፣ ነፃነት እና ንብረት በህጋዊ መንገድ ሊያጠፋ አይችልም፡፡

ይህን የመሰለ በሁለቱም መንገዶች የሚፈጠር የጉልበትን ባፈንጋጭነት መጠቀም ከተነሳንበት የመንደርደሪያ ሃሳብ ጋር ይጋጫል፡፡ ጉልበት ወይም ኃይል የተሰጠን የራሳችንን የግል መብቶቻችንን እንድንጠብቅበት ነው፡፡ ኃይል የተሰጠን የወንድሞቻችንን ከኛው እኩል የሆኑ መብቶችን ለማጥፋት ነው ያለው ማን ነው? የትኛውም ግለሰብ በግሉ በህጋዊ መንገድ ጉልበት ተጠቅሞ የሌሎችን መብት ሊያጠቃ ስለማይችል፣ ከተደራጀ የግለሰብ ጉልበት ስብስብ የሆነው የጋራ ኃይልስ ላይ ተመሳሳይ መርህ ተፈፃሚ መሆኑ ምክንያታዊ አይደለም?

ይህ እውነት ከሆነ ከሚከተለው ሃሳብ የተሻለ የተረጋገጠ እውነት አይኖርም፤ ህግ የተደራጀ የግለሰብ መብት ህጋዊ መከላከያ ነው፡፡ የግለሰብ ጉልበትን የተካ የጋራ ጉልበት ነው፡፡ ይህ የጋራ ጉልበት  ማድረግ የሚችለው ግለሰቡ ባለው  ተፈጥሯዊ እና ህጋዊ መብት በጉልበቱ  ሊያደርግ የሚችለውን ብቻ ነው፡- ሰውነትን፣ ነፃነትን እና ንብረትን መጠበቅ፤ የሁሉንም መብት ማስጠበቅና ፍትህ በሁላችን ላይ እንዲገዛ ማድረግ ነው፡፡

ፍትሃዊ እና ፅኑ መንግስት

      በዚህ መሰረት ሃገር ከተመሰረተ በሃሳብም ሆነ በድርጊት ስርዓት በህዝቡ መካከል የሚሰፍን ይመስለኛል፡፡ ይህን የመሰለው ሃገር ፖለቲካዊ አደረጃጀቱ ምንም ሆነ ምን ልናስበው ከምንችለው መንግስት ሁሉ በላይ የተሻለ ቀላል፣ ለመቀበል የሚቀል፣ ቆጣቢ፣ ገደብ የተበጀለት፣ ጨቋኝ ያልሆነ፣ ፍትሃዊ እና በቀላሉ የማይፈርስ የሚሆን ይመስለኛል፡፡  

      በዚህ መሰል አስተዳደር ስር እያንዳንዱ ሰው የህልውናው ሁሉም ልዩ ጥቅሞችም ሆኑ ሁሉም ኃላፊነቶች እንዳሉት ይገባዋል፡፡ ሰውነቱ (person) እስከተከበረለት ድረስ፣ በሥራው ነፃ እስከሆነ ድረስ፣ የድካሙ ፍሬ ከሁሉም ኢፍትሃዊ ጥቃቶች እስከተጠበቀለት ድረስ ማንም ሰው ከመንግስት ጋር ሙግት አይኖረውም፡፡ ስኬታማ ስንሆን ለስኬታችን መንግስትን ማመስገን አይጠበቅብንም፡፡እንዲሁም በተቃራኒውም ገበሬዎች ለበረዶው እና ለውርጩ መንግስትን ሊተቹ እንደማይችሉ ሁሉ ካልተሳካልን ለራሳችን እድለ መጥመም መንግስትን ተጠያቂ ለማድረግ አናስብም ነበር፡፡ የመንግሰት መኖር የሚታወቀን በዚህ የመንግስት ፅንሰ ሃሳብ አማካኝነት በሚገኘው ሊተመን የማይችል የደህንነት በረከቶች ብቻ ይሆን ነበር፡፡

      በተጨማሪም በግል ጉዳዮች ጣልቃ ለማይገባው መንግስት ምስጋና ይድረሰውና ፍላጎቶቻችን እና የፍላጎቶቻችን መሟላት ምክኒያታዊ በሆነ መንገድ አብረው ይዳብሩ ነበር፡፡ ድሃ ቤተሰቦች ዳቦ ከማግኘታቸው በፊት ስነፅሁፋዊ መመሪያ ሲሹ አንመለከትም፡፡ የከተሞች ክልል በገጠሩ ፍልሰት በህዝብ ሲጣበቡም ወይም የገጠሩ ክልል በከተሞች ፍልሰት ሲጨናነቅ አንመለከትም ነበር፡፡ በህግ አውጪው ውሳኔ ምክንያት የሚፈጠር ታላቅ የካፒታል፣ የስራ ሃይል እና የህዝብ ፍልሰት አንመለከትም ነበር፡፡

      በእነዚህ መንግስት የሚፈጥራቸው ፍልሰቶች ምክንያት የመኖራችን ምንጭ ያልተረጋገጠ እና የማያስተማምን ሆኗል፡፡ ከዚህም አልፎ እነዚህ ድርጊቶች የመንግስትን ኃላፊነት በማብዛት ሸክም ይጨምሩበታል፡፡

የህጉ ፍፁም ማፈንገጥ 

      የሚያሳዝነው ግን ህግ በየትኛውም መንገድ ራሱን በተገቢ ዓላማዎቹ ላይ ብቻ ወስኖ አላስቀረም፡፡ ተገቢ ዓላማውን ሲያልፍ በማይረቡ ወይም አከራካሪ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ብቻ አይደለም፡፡ ህግ ከዚህ ብዙ ርቆ ሄዷል፤ ከራሱ አላማ ፍፁም ተቃራኒ በሆነ መንገድ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ህግ የራሱን ግብ ለማፍረስ ጥቅም ላይ ውሏል፤ ሊጠብቀው ይገባ የነበረውን ፍትህ ለመደምሰስ፣ ሊያስከብራቸው ይገባ የነበረውን መብቶች ለመገደብ እና ለማጥፋት ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ ህግ የጋራ ሃይልን ካለምን ችግር በሌሎች ሰውነት፣ ነፃነት እና ንብረት ለመጠቀም ለሚፈልጉ ይሉኝታ ቢሶች መገልገያ ሆኗል፡፡ ብዝበዛን ለመጠበቅ ብዝበዛን ወደ ትክክልነት ለውጦታል፡፡ እንዲሁም ህጋዊ መከላከልን ለመቅጣት ህጋዊ መከላከልን ወደ ወንጀልነት ቀይሮታል፡፡

      ይህ የህግ አፈንጋጭነት እንዴት ሊሳካ ቻለ? ውጤቱስ ምን ሆነ?

      ህግ ያፈነገጠው በሁለት ምክንያቶች ተፅዕኖ ነው፤ ዓይን ያወጣ ስግብግብነት እና የተሳሳተ በጎ አድራጎት፡፡ በቅድሚያ ስለመጀመሪያው እንነጋገር፡፡

በቀጣዩ ልጥፍ (ፖስት) የፍሬደሪክ ባስትያት ዘ ሎው የተሰኘ መድብል የህግ ማፈንገጥን እውን ያደረው ምን እንደሆነ እና ሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባህርይ ጋር ያለውን ትስስር ያስዳስሰናል፡፡


picture credit

gio, CC0, via Wikimedia Commons

Comments