የፍትህ ሥርዓቱ ግብ ፍትህ ሣይሆን ሕግ እና ሥርዓት ነው የምለው ደስ እያለኝ ሳይሆን እያዘንኩ ነው፡፡ ይህን ጉዳይ ይበልጡን ባሰብኩት ቁጥር ፍትህ በሰው ልጅ እጅ አለፍ አለፍ እያለች ያጋጣሚ ልትገኝ ትችል ይሆናል እንጂ ትክክለኛ ፍትህ መስጠት ልዕለ ሰብ ሃይል ጣልቃ ገብነት ይፈልጋል፡፡
በሕግ ሞያ ባለሟልነት መስራት የራሱ ፈተናዎች፣ የራሱ ግራመጋባቶች (confusion and dilemma) አለው፡፡ አንዳንዴ የሕግ ሞያዬ ከሰው ልጅ ሁሉ ጋር በጅምላ ያጣላኛል፤ ፀቤ የማይታይ ነው፤ ልቦናዬ ውስጥ ነው፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ ፀቤ ከራሴ ጋር ይሆናል፡፡ አንድ የህግ ባለሞያ በፍትህ ሥርዓቱ ውስጥ ያለውን ሚና ለመወጣት በሚያደርገው ጥረት ከራሱም ጋር ሳይቀር ይጣላል፡፡ ዳኛ፣ ጠበቃ፣ ነገረፈጅ ወይም ዐቃቤ ሕግ ሆኖ የተሰጠውን ሚና ለመወጣት ሲባትል ከራሴ ጋር ተጣልቼ አላውቅም የሚል ካለ ወይ ህሊናው መጅ አውጥቷል ካልሆነም የሰው ልጅ ድክመት ያልተጣባው የፍትህ ሥርዓቱን በተአምር የሚዘውር መልአክ ወይም ልቦናው ማመዛዘኑን የተነጠቀ አጋንንት ነው ስል መሞገቴ አይቀርም፡፡
ያለፈው ሰሞን አንድ ችሎት ውስጥ ነበርኩ፡፡ የተረጋጋ ባለጉዳዮችን በአክብሮት የሚያስተናግድ ሰብአዊነቱን በቀላሉ ልገነዘብለት የቻልኩት ዳኛ ተሰይሟል፡፡ ሦስት ጠበቆች እና አንድ ዐቃቤ ህግ ከፊቱ ቆመው ሙሉ ሰዓት ሊሞላ ጥቂት ለቀራቸው ደቂቃዎች የወከሉትን ወገን ፅድቅ ሲያገዝፉ የሌላኛውን ወገን ኃጢያት ሲያገኑ ቆዩ፡፡
ጉዳዩ የመኖሪያ ቤትን የተመለከተ የፍትሃብሄር ጉዳይ ነው፡፡ በክርክሩ ሂደት ከሣሽ የሆኑት ባልቴት ከጠበቃቸው ጀርባ ተቀምጠው፣ ወደ ምድር አቀርቅረው ድምፅ ሳያወጡ ያነበንባሉ፡፡ ፀሎት መስሎኝ ነበር፡፡ በኋላ ግን ደረቅ ፀሎት ሳይሆን በእንባ የረሰረሰ ምልጃ እንደሆነ ታዘብኩ፡፡
እኔም ተራዬ እስኪደርስ የምጠብቅ የሕግ ባለሟል ጠበቃ ነኝና የሁሉንም ወገን ክርክር በአርምሞ ስመዝን ነበር፤ ከሳሽ ተስፋ ያላቸው አይመስልም፡፡ ከሣሽ ባልቴት ግን እርጥብ፣ ድምፅ አልባ ልመናቸውን አላቋረጡም፤ ተስፋቸውን ፈጣሪያቸውን ያደረጉ ይመስላል፡፡ መኖሪያ ቤታቸው ወኪል ነኝ ባለ ሰው ተሸጦ፤ ሲገላበጥ ቆይቶ ሁለተኛ ወይም ሦስተኛ ገዢ እጅ ደርሷል፡፡
ወደ ክርክሩ መገባደጃ ችሎቱ ቀጠሮ ለመስጠት እያኮበኮበ ሳለ እኒህ ሰው ከተቀመጡበት በዝግታ ተነሱ፤ የምናገረው አለ አሉ፡፡ ጠበቃቸውም ቀጠል አርጋ ለመናገር እንዲፈቀድላቸው ችሎቱን ጠየቀች፡፡ አንደኛው ባላጋራ ጠበቃ ተቃወመ፤ ተወክለው ጠበቃቸው አፍ ሁናላቸዋለች፤ ሂደቱም ተጠናቋል ሲሉ ሞገተ፡፡ ዳኛው ለጉዳዩ በሩቁ የሚቀርብ የሥነ ሥርዓት ሕግ ጠቅሰው ባልቴቷ እንዲናገሩ ፈቀዱ፡፡ ከ10 ዓመታት በላይ የፍርድ ቤት ቆይታዬ በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ችሎቶች ጠበቃው ተጠይቆ ለችሎቱ ያልመለሰው ጥያቄ የለምና፤ ሁሉም ወገን ተራውን ተከራክሮ አጠናቋልና፤ ሥነ ሥርዓታዊ አይደለም ሲሉ የከለከሉ ዳኞች ስታዘብ ስለኖርኩ እኒህ ዳኛ ሰብዓዊነታቸው የሚጫናቸው የሕግ ሰው ስለመሆናቸው ቀደም ስል የገመትኩትን አረጋገጥኩ፡፡
ባልቴቷ መናገር ጀመሩ፡፡ ንግግራቸው በዝምታ ሲያነበንቡ የነበረውን በእንባ የረሰረሰ ፀሎት ከለሆሳስ ወደ ጎላ ድምፅ፣ ከፈጣሪ ወደ ዳኛው አድርገው የደገሙበት እንጂ ክርክር ሊባል የሚችል ንግግር አልነበረም፤ ልመናና ተማፅዕኖ ነው፡፡ ዳኛውም ታዳሚውም ርህራሄ ፊታቸው ላይ እየተነበበ ማዳመጣቸውን ቀጠሉ፡፡
በንግግራቸው ጣልቃ ከባልቴቷ ባላንጣ ጠበቆች ሌላኛው ተቃውሞ አሰማ፡፡ የባልቴቷ ንግግር ስሜትን በመኮርኮር የችሎቱ ዳኛ ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር የተቃጣ ነው ሲል ሞገተ፤ ደግሞም በእኔ እምነት ተገቢ ተቃውሞ ነበር፡፡ ይህ ጠበቃ ባልቴቷን ከንግግራቸው ያናጠባቸው ጋኔን ስለሰፈረበት ነው? የርህራሄ ዘር ልቡ ውስጥ ስላልተፈጠረበት ነው? በፍፁም፡፡ ከችሎት በኋላ ውሎውን መለስ ብሎ ሲያስበው በችሎት እንደነበረው እንደማንኛውም ታዳሚ ስለ ሴትዬዋ ልቡ በሃዘን ሊሞላ እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ ነገር ግን ሥራውን መስራት ነበረበትና አጥብቆ ተቃወመ፡፡ የባልቴቷም ጠበቃ ደንበኛቸውን ደግፈው ተቃውሞውን ተቃወሙ፡፡
ዳኛውስ? ዳኛው ለጥቀው የተናገሩት ነው ይህንን ታሪክ ላንባቢ እንዳካፍል የገፋኝ፡፡ ዳኛው በዚያ ቀንም ሆነ ከዛ ቀን ቀደም ችሎቱን ሲመሩ ዘወትር በሚታይባቸው ሰብዓዊነት የተላበሰ ድምፀት የሚከተለውን አሉ፡- “መቼም ሁላችሁም ባለሞያዎች ናችሁ፡፡ ታውቁታላችሁ፡፡ ውስጣችን የሚነግረን ቢኖርም ስሜታችን ተፅዕኖ እንዲያደርግብን አንፈቅድም፡፡ ሕግንና የቀረበውን ማስረጃ ብቻ ተመስርተን ነው የምንወስነው” አሉ፡፡
በእኔ እይታ ይህ ንግግራቸው ትክክልም ስህተትም ነው፡፡ ከንግግሩ ትክክልም ስህተትም መሆን በላይ ግን በሕግ ባለሟሎች ህይወት ውስጥ ደግሞ ደጋግሞ የሚገጥምን ፈተና ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡
ስሜታችን በአብዛኛው የድብቁ አእምሯችን (sub-conscious mind) መልዕክት ነው፤ ድብቁ አዕምሯችን እውነት ነው፣ ፍትሃዊ ነው ያለውን አቋም እያሳወቀን ነው፡፡ ንቁው አዕምሯችን (conscious mind) ግን ከድብቁ አዕምሯችን መልዕክት ጋር የሚጋጭ አመክንዮ ሊደረድር ይችላል፤ ሕግን ጠቅሶ ድብቁ አዕምሮ የበየነውን፣ ሕግ አይፈቅድም ሊለን ይችላል፤ ከሳሽ ሆነ ያሉትን ደረደሩ እንጂ ከገዛ ቃላቸው ውጪ ማስረጃ የላቸውም እኮ ሊለን ይችላል፡፡ ፈተና ነው! ነገሩ ይበልጥ ሲከብድ ደግሞ የድብቁ አዕምሯችን ብይን እውነት ስለመሆኑ በሕይወት ልምድ ወይም በፍርድ ቤት በማስረጃነት ሊቀርብ በማይችል ሁኔታ ልናረጋግጥ እንችል ይሆናል፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ለወደቀ ዳኛ ፈተናው ይታያችሁ!
በዚህ ሃሳብ እየተብሰለሰለ ሲጓዝ ተደናቅፎ ወድቆ ይሆን? ከሚበር መኪና ለጥቂት ተርፎ ይሆን? ማታ እቤቱ ገብቶ ልጁ አባዬ ስትለው ምላሽ ነስቷት ይሆን? ከቢሮው እለት ተእለት ተሸክሞት የሚመጣው መብሰልሰሉ ትዳሩ መሃል ንፋስ አስገብቶ ይሆን? ሕግን ተከትሎ ከግል እምነቱ ጋር የሚጋጭ ውሳኔ ሰጥቶ ራሱን እስኪጠላው ታዝቦት ይሆን? እዩልኝ ፈተናውን!
እነዚህ ሁኔታዎች ብዙ ጊዜ ሃሳብ ላይ ይጥሉኛል፡፡ ፈተናው ሞያው ላይ ያለ ይበልጡን ይገባዋል፡፡ ለዚህ ነው ሰው ሆነን ፍጽም ፍትህን ማስፈን እሩቃችን ስለሆነ የፍትህ ስርዓቱ ዋነኛ ግብ ስሙ “ፍትህ” ቢባልም “ሕግና ስርዓት (law and order)” ነው የምለው፤ እግረ መንገዱን ፍትህ ከሰፈነ እድለኝነት ነው፡፡
ጤና ይስጥልኝ


Comments
Post a Comment