በፍርድ ቤት የሚደረጉ ክርሮች እና የሚሰሙ ምሥክሮች በተለይ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመቅረፀ ድምፅ ይያዛሉ፡፡ በፌዴራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤቶች ግን አብዛኖቹ ክርከሮች እና የምስክሮች ቃል በዳኞች በእጅ ይፃፋል፡፡
በእነዚህ ችሎቶች ምሥክሮቻችሁ ያስረዱላችሁ ጭብጦች ሳይመዘገብላችሁ ቀርቶ
ያውቃል? በመስቀለኛ ጥያቄያችሁ ያስጣላችሁት ነጥብ በፍርድ ቤት መዝገብ ውስጥ ሽታው ጠፍቶባችሁ ያውቅ ይሆን? በስር ፍርድ ቤት
በምሥክሮች ስለመነገሩ እርግጠኛ የሆናችሁበትን ፍሬ ነገር ተመስርታችሁ ይግባኝ ጠይቃችሁ በይግባኝ ችሎቱ “እርሶ በምሥክሮች ተነግሯል
ቢሉም ከስር ፍርድ ቤት መዝገብ የሚሉትን አያሳይም” ተብላችሁ ኩም ብላችሁ ታውቃላችሁ?
እኔን ገጥሞኝ ያውቃል!
ግን ለምን???
አንድ ጠበቃ ወዳጄ የገጠማትን አጫወተችኝ፡፡
በፍርድ ቤት መድረክ ግራ ቀኙ ምስክሮቻቸውን አቅርበው እየተፋለሙ ነው፡፡
የምተርከው ገጠመኝ የተፈጠረው የወዳጄ ባላጋራዎች ምሥክር ቀርቦ በሚሰማበት
ወቅት ነው፡፡ ምሥክሩ ባቀረበው ጠበቃ ሲጠየቅ ቆይቷል፡፡
ምሥክሩን ያቀረበው ጠበቃ የሚጠይቀው የጥያቄ ዓይነት ዋና ጥያቄ ይባላል፤
በዋና ጥያቄ የሚቀርቡት ጥያቄዎች ምስክሩ የሚያስረዳውን ጉዳይ የመንገር ያህል እንዲሆኑ አይፈቀዱም፤ መሰል ጥያቄዎች መሪ ጥያቄ
ይባላሉ፡፡ በተቃራኒው ደንበኛውን ወክሎ ምሥክሩን ያቀረበው ጠበቃ ዋና ጥያቄ አቅርቦ እንደጨረሰ ባላንጣው ጠበቃ የምስክሩን ቃል
ተዓማኒነት ለማሳጣት ወይም ለማፍረስ ይጠይቃል፤ ይህ የጥያቄ ዓይነት መስቀለኛ ጥያቄ መጠሪያው ነው፡፡
በመስቀለኛ ጥያቄ ወቅት ምሥክሩን ያቀረበው ጠበቃ ከጠየቃቸው ወይም ምሥክሩ
ካብራራው ርዕሰ ጉዳዮች ወይም ከእነዚህ ርዕሰ ጉዳዮች ጋር በቀጥታ ከሚገናኙ ፍሬ ነገሮች ውጪ መጠየቅ አይቻልም፡፡
እናም ወዳጄ ባላጋራ የስራ ባልደረባዋ የገዛ ምስክሩን ዋና ጥያቄ ጠይቆ
ሲጨርስ የመስቀለኛ ጥያቄ ፍላፃዎቿን ወደ ምሥክሩ ታስወነጭፍ ገባች፡፡ ተከራካሪዋ ጠበቃ፣ ከጠበቃ እንደሚጠበቀው ጋሻውን አንግቦ
ካልተገቡ ፍላፃዎች ምሥክሩን ሊጠብቅ አድብቶ፣ ሁለቱ ጠበቆች በፍትህ መድረክ የሞያ ቲያትራቸውን ሲጫወቱ ቆዩ፡፡
ወዳጄ የሰነዘረችው አንድ ጥያቄ ላይ ባላንጣዋ ጠበቃ ጋሻውን አነሳ፤ ተቃወመ፡፡
“ያቀረበችው ጥያቄ እኔ ዋና ጥያቄ ላይ ባላነሳሁት ጉዳይ ላይ ነው” ሲል ጥያቄው እንዲሰረዝ፣ ምሥክሩም ለጥያቄው መልስ እንዳይሰጥ
ችሎቱን ተማፀነ፡፡
የችሎቱ ዳኛ ምሥክሩ ሲያስረዳ የመዘገቡትን መለስ ብለው አገላበጡ፡፡
በአከራካሪው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ምስክሩ ስለመመስከሩ የሚያሳይ ያሰፈሩት
ቃል የለም፡፡ ይህን ግንዘቤ የወሰዱት ዳኛ ወደ ጠበቃዋ ዞር ብለው ጥያቄሽ በዋና ጥያቄ ባልተነሳ ጉዳይ ላይ የቀረበ ስለሆነ እርሽው
አሏት፡፡ ወዳጄ በእግዜር ብላ አልተቀመጠችም፤ እረ መስክሯል ፣ እንደውም ምስከሩ ሲያስረዳ የያዝኩትን ማስታወሻ ለችሎቱ እንዳነብ
ይፈቀድልኝ ስትል ስትር ብላ ፈቃድ ጠየቀች፡፡ ተፈቅዶላት አነበበችው፡፡
በችሎቱ
መዝገብ በጉዳዩ ላይ ተመስክሮ የተያዘ ቃል የለም፤ በተቃራኒው ጠበቃዋ
በማስታወሻዋ ከትባዋለች፡፡ ጠበቃዋ ተፈቅዶላት በማስታወሻዋ ያሰፈረችውን ፍሬ ነገር በንባብ አሰምታ እንደጨረሰች ደግማ ፈቃድ ሳትጠይቅ
ምስክሩን ያነበበችውን ተናግሮ እንደሆነ ጠየቀችው፡፡ ምስክሩ ሳያቅማማ የእሷ ማስታወሻ ትክክል መሆኑን አረጋገጠላት፡፡ ችሎቱም ተቃውሞ
የቀረበበትን ጥያቄዋን እንድትጠይቅና እንዲመለስላት ፈቀደላት፡፡
ዳኞች የምሥክር ቃል በእጃቸው ሲመዘግቡ መሰረታዊ ነጥቦችን ሳያሰፍሩ ሊያልፉ
እንደሚችሉ ጠበቃዋ ወዳጄ ከገጠማት ሁነት የችግሩን ሃቀኝነት መገንዘብ
እንችላለን፡፡
በእርግጥ ወዳጄን የገጠሟት ዳኛ ስህተታቸውን ለመቀበል የጀገኑ ከአርቴፊሻል ክብር ይልቅ ትክክለኛ ፍትህ መሰጠቱ የሚገዳቸው ስለሆኑ እውነተኛ ክብር ይገባቸዋል፡፡
ግን ለምን?
ለምን የምሥክር ቃል በእጅ በሚጽፉባቸው ችሎቶች ዳኞች በችሎት የተነገሩ ፍሬ ጉዳዮችን በመዝገብ
ሳያሰፍሩ ይቀራሉ?
1.
ሰው ስለሆኑ
ያስነበብኳችሁ እውነተኛ ገጠመኝ ከባለ ታሪኩ
ዳኛ ባህርይ አንፃር ሲፈተን ዳኞችም ሰው ስለሆኑ፤ መፃፍም ሆነ መስማት
ስለሚደክም የሚል መልስ ይሰጠናል፡፡
ሰው ስለሆኑ ይደክማሉ፤ ይሰለቻሉ፣ ሲያልፍም ይሰንፋሉ፤ እንደማናችንም፡፡
በድካም ሳይሰሙት ሊያልፉ፣ በመሰልቸት ከንግግሩ እኩል መፃፍ ሊሳናቸው ይችላል፡፡ የራሱ ጉዳይ እያለ እየዘለለ የሚጽፈውም ላይ ሊጥለን
ይችላል፡፡
2.
ሆን ብለው
በዳኝነት ሥርዓቱ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በየትኛውም የሀገራችን የተገነባ ሥርዓት
ውስጥ ብልሹ አሰራር አለ፡፡ ስለሆነም ከብልሹ ሥነ ምግባር ያለው ዳኛ
ከውሳኔው በኋላ (በፊትም ሊሆን ይችላል፣ እንደመደራደር አቅሙ) የሚቀርብለትን እጅ መንሻ አስቦ ለሚፈልገው ውሳኔው እንቅፋት
ሊሆኑ ይላሉ ያሏቸውን ነጥቦች ሆን ብሎ ቀነጣጥቦ ሊያስቀር ይችላል፡፡
3.
ድብቅ አድሎ በድብቅ ልቦና
አንዳንዴ መድሎ (bias መድሎ ነው የሚባለው?) ሳናውቀው የድብቁን ልቦናችንን
ፈቃድ ሊፈጽም ይችላል፡፡ ተግባሩን አልፎ ሲመለከት በራሱ ሊያዝን ይችላል፡፡ የድብቁን ልቦና አድሎ አጋጣሚ ወይም አስገዳጅ ሁኔታ
እንዲገነዘበው ያደረገው ዳኛ በራሱ ሊያዝን ቢችልም፤ ብዙ ጊዜ ላይስተካከል የተጣመመ ሊሆን ይችላል፡፡
መፍትሄ?
ምን ይሻላል?


Comments
Post a Comment