Skip to main content

የተሻሻለው የጸረ ሙስና ልዩ የሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ አዋጅን ለማሻሻል የወጣው አዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ ዙሪያ የቀረበ መነሻ የሆነ አጭር የሕግ ማስታወሻ

"In Claris non fit interpretatio." (When the text is clear, no interpretation is needed.) 






በጠበቃ ዘርአይ ወልደሰንበት

መግቢያ፣

ይህ አጭር መነሻ የሆነ የሕግ ማስታወሻ በተሻሻለው የጸረ-ሙስና ልዩ የሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ ማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ ላይ የተደነገገውን በዋስትና የመፈታት መብት ገደብ ስፋትና ወሰን ዙርያ ያተኮረ ሲሆን፤ በተለይም በዚሁ ድንጋጌ ስር ስለተመለከተው የዋስትና መብት እና የዋስትና ክልከላ ከጅምሩ በተለያየ ምክንያት በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ያልተያዙ ሰዎች፣ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ተይዘው በፖሊስ ወይም በፍርድ ቤት ዋስትና ከእስር ከተለቀቁ በኋላ በዚያው በተለቀቁበት ጉዳይ ላይ በሙስና ወንጀል የተከሰሱ ሰዎችና በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች ላይ የሚተገበርበትን ሕጋዊ ሁኔታ አስመልክቶ የውይይት በር ለመክፈት በማሰብ በዝርዝር የመጀመሪያ ምልከታና ዳሰሳ ለማድረግ ተሞክሯል። ይህንን የሕግ ማስታወሻ ለመጻፍ ያነሳሳኝ ዋና ምክንያቶች በቅርቡ አንድ ደንበኛዬ የሆነ ሰው በሙስና ወንጀል ክስ የቀረበበት መሆኑን ከሌላ ሰው ከሰማ በኋላ ጉዳዩን አጣርቶ የሙስና ወንጀል ክሱ የቀረበበት የሙስና ወንጀል ችሎት ዘንድ ባልተያዘበትና ባልታሰረበት ሁኔታ ከውጭ በገዛ ፍቃዱ በቀረበ ጊዜ የጸረ ሙስና ወንጀል ችሎቱ የአዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 3(1) ድንጋጌን መሠረት በማድረግ በቂሊንጦ ማረፍያ ቤት ሆኖ ጉዳዩን እንዲከታተል ሲል በቅርቡ የሰጠው የዋስትና ክልከላ ትእዛዝ/ውሳኔ፣ በዚህ ረገድም በፌደራል ፍርድ ቤቶች ዘንድ እንዲህ ዓይነት ክርክር ሲነሳ ጨርሶ ወይም እምብዛም የማይታይ በመሆኑ እና በዚህ ጉዳይ ላይ ያተኮረ የሕግ ጽሁፍና የሰበር ውሳኔ የሌለ ወይም እጥረት ያለ መስሎ የታየኝ መሆኑ ናቸው።

1.  የአዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ የተፈጻሚነት ወሰን በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች ላይ ብቻ የተገደበ መሆን ወይንም አለመሆኑን በተመለከተ፣                                                                                                                                                                                 

በዚህ ክፍል ውስጥ የአዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ የተፈጻሚነቱ ወሰን በሙስና ወንጀል የተያዙ ሰዎች ላይ ብቻ የተገደበ መሆን ወይንም አለመሆኑን በሚመለከት በዝርዝር ምልከታና ዳሰሳ ተደርጓል። ጠበቃ ሙልጌታ በላይ በድህረ ገጽ ባሳተመው አጭር የሕግ ጽሁፍ ላይ በተሻሻለው የፀረ-ሙስና ልዩ የሥነ ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ ማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ ላይ በግልፅ እንደተደነገገው ከ10 ዓመት በላይ በሆነ ጽኑ እስራት በሚያስቀጣ የሙስና ወንጀል የተያዘ ወይም የተከሰሰ ሰው በሕግ የዋስትና መብቱን ያጣል በማለት ድምዳሜ ሰጥቷል፡፡[1] ይህም ማለት የአዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ በሙስና ወንጀል በተያዙ ሰዎች ላይ ብቻ ሳይሆን በሙስና ወንጀል ባልተያዙ የተከሰሱ ሰዎችም ላይ ተፈጻሚነት አለው ማለት ነው። ሆኖም ግን የተሻሻለው የጸረ-ሙስና ልዩ የሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ (ማሻሻያ) አዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ እንዳለ እንዲህ ይነበባል:-

"በሙስና ወንጀል የተያዘ ሰው በዋስ እንዲለቀቅ ለፍርድ ቤት ማመልከት ይችላል፤ ሆኖም የተከሰሰበት ወይም የተጠረጠረበት ወንጀል ከአሥር ዓመት በላይ በሆነ ጽኑ እስራት ሊያስቀጣ የሚችል ከሆነ በዋስትና መለቀቅ አይችልም። ከአራት ዓመት በላይ እና ከአስር ዓመት በታች የሚያስቀጡ ተደራራቢ ወንጀሎች ሲኖሩም እየተደመሩ ከአስር ዓመት በላይ የሚያስቀጣ ከሆነ ዋስትና ይከለከላል።"[2]

 

ከዚህ በላይ የተመለከተው የአዋጁ አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ የመጀመሪያው ዓረፍተ ነገር ላይ የደነገገው መሠረታዊ ደንቡ/መርሁን ሲሆን፣ ሁለተኛው ዓረፍተ ነገር ደግሞ የደነገገው ልዩ ሁኔታውን ነው። ይህ እንዳለ ሆኖ፣ የአዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ ተፈጻሚነት ያለው በሙስና ወንጀል (ተጠርጥረው) በተያዙ ሰዎች ላይ ብቻ ወይንስ በሙስና ወንጀል (ተጠርጥረው) ባልተያዙ የተከሰሱ ሰዎች ላይ ጭምር መሆን አለመሆኑን በተመለከተ ከዚህ በታች በዝርዝር ዳሰሳ ተደርጓል። ይኸውም:-

1.1. ከዚህ በላይ የተጠቀሰው የአዋጁ አንቀጽ 3(1) ላይ በግልጽ የተመለከተዉ "በሙስና ወንጀል የተያዘ ሰው" የሚለው ሐረግ የሚያመለክተዉ በልዩ ሥነ ሥርዓት ሕጉ መሠረት በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው "የተያዙ ሰዎችን" ብቻ ነው። "በሙስና ወንጀል የተያዘ ሰው" ማለት በአዋጅ ቁጥር 881/2007 ውስጥ በተደነገገው ማናቸውም የሙስና ወንጀል ተጠርጥሮ በሕግ አስከባሪ አካላት በኩል በሕጋዊ መንገድ የመንቀሳቀስ ነጻነቱ ተነፍጎ/ተገድቦ የተያዘ/በቁጥጥር ስር የዋለ/ እና ወደ እስር ቤት/ማረፍያ ቤት የተወሰደ ሰው ማለት ነው። ከዚህም አንጻር፣ ድንጋጌው በሙስና ወንጀል የተያዙ ሰዎች በመርሕ ደረጃ በዋስትና የመለቀቅ ወይም የመፈታት /ከእስር የመውጣት/ ሕጋዊ መብት እና በልዩ ሁኔታ ደግሞ ዋስትና ስለሚከለከሉበት ሕጋዊ ሁኔታ ነው የደነገገው።

1.2. እንደዚውም፣ "በዋስ እንዲለቀቅ" የሚለው ሐረግ የሚያመለክተውም የአዋጁ አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ ተፈጻሚነት ያለው በሙስና ወንጀል የተያዘ ሰው በዋስ እንዲለቀቅ ለፍርድ ቤት ማመልከቻ ባቀረበ ጊዜ ተፈጻሚ የሚሆን መሆኑን ነው። ምክንያቱም "በዋስ እንዲለቀቅ" የሚለው ሐረግ ቀደም ብሎ መያዝን ወይም በቁጥጥር ስር መዋልን ታሳቢ የሚያደርግ በመሆኑ ነው። በሙስና ወንጀል የተያዘው ሰው በዋስ የሚለቀቀውም ከመያዝ ወይም ከእስር እንጂ ካለመያዝ ወይም ካለመታሰር አይደለም።

1.3. እንዲሁም በዚህ ድንጋጌ ላይ የተቀመጠው ድርብ ነጠላ ሰረዝ(፤[3]) የሚያመለክተው "በሙስና ወንጀል የተያዘ ሰው በዋስ እንዲለቀቅ ለፍርድ ቤት ማመልከት ይችላል" የሕጉ መርሕ መሆኑን ነው። ከድርስ ነጠላ ሰርዙ(፤) በኋላ የተመለከተው "ሆኖም የተከሰሰበት ወይም የተጠረጠረበት ወንጀል ከአሥር ዓመት በላይ በሆነ ጽኑ እስራት ሊያስቀጣ የሚችል ከሆነ በዋስትና መለቀቅ አይችልም።" የሚለው ዓረፍተ ነገር ደግሞ ልዩ ሁኔታ መሆኑን ያመለክታል። በዚህ መንገድ ሁለቱ ዓረፍተ ነገሮች ሎጂካሊ በዐውደ ጽሁፉ ውስጥ የተያያዙና ተዛማጅ የሆኑ ነገሮች መሆናቸውን የሚያሳይ ሆኖ በምትኩ አራት ነጥብን በመጠቀም ሊከሰት የሚችለውን አሻሚነት ለማስወገድ የገባ አገናኝ/አያያዥ ሥርዓተ ነጥብ ነው። ከዚህም አንጸር፣ አዋጁ አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ የአማርኛው ቅጂ ሁለተኛው ዓረፍተ ነገር ከመጀመሪያው ዓረፍተ ነገር ተነጥሎ ብቻውን የቆመ ሃሳብ አይደለም።

1.4. በተጨማሪ፣ አዋጁ አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ የአማርኛው ቅጂ ሁለተኛው ዓረፍተ ነገር "ሆኖም የተከሰሰበት ወይም የተጠረጠረበት ወንጀል ከአሥር ዓመት በላይ በሆነ ጽኑ እስራት ሊያስቀጣ የሚችል ከሆነ በዋስትና መለቀቅ አይችልም።" የሚል ሲሆን የዚሁ ድንጋጌ የእንግሊዝኛው ቅጂ ሁለተኛው ዓረፍተ ነገር ደግሞ "provided, however, that an arrested person charged or suspected with a corruption offense punishable for more than 10 years shall not be released on bail." ይላል። በዚህ የእንግሊዝኛው ቅጂ ላይ "that an arrested person." በሚል ይበልጥ ግልጽ በሆነ ሁኔታ ተመልክቷል። ከዚህም አንጸር፣ አዋጁ አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ የመጀመሪያው ዓረፍተ ነገርም ሆነ ሁለተኛው ዓረፍተ ነገር የተያያዙና የሚደነግጉትም በሙስና ወንጀል የተያዘ ሰው በፍርድ ቤት በዋስ/በዋስትና ስለሚለቀቅበት እና ሊለቀቅ ስለማይችልበት ሕጋዊ ሁኔታ ብቻ መሆኑን መረዳት ይቻላል። ስለዚህም በአዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 3(1) ላይ የዋስትና ክልከላ የተደረገው በሙስና ወንጀል ተጠርጠረው ለተያዙ ሰዎች ብቻ ነው። ምክንያቱም እስር ከሌለ፣ መለቀቅ ብሎ ነገር አይኖርም። በሌላ አነጋገርም፤ መያዝ ሳይኖር ቅድመ ትሪያል እስር/ከፍርድ በፊት እስር ሊኖር አይችልም። በመሆኑም መያዝ (Arrest) ከእስር (detention) በፊት ይመጣል፤ ይህም በወንጀል ሕጉ እና በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 17፣ 19(6)ና 20(3) ላይ የተጠበቀ ሕገ መንግስታዊ የሆነ መርህ ነው።

1.5. ከዚህ በተጨማሪም፣ የድንጋጌዉ የአማርኛ ቅጂ አርዕስት "በሙስና ወንጀል ተጠርጥረዉ ስለተያዙ ሰዎች በዋስትና የመፈታት መብት" የሚል ሲሆን የዚሁ ድንጋጌ የእንግሊዝኛው ቅጂ ርእስ ደግሞ "The Right to Bail of Arrested persons on Corruption Offences" ይላል። ከዚህም የድንጋጌው አርዕስት መገንዘብ እንደሚቻለው ድንጋጌው የሚናገረው በሙስና ወንጀል ተጠርጥረዉ የተያዙ ሰዎች በዋስ/በዋስትና/ ከእስር ስለሚለቀቁበት/ስለሚፈቱበት እና ስለማይለቀቁበት/ስለማይፈቱበት ሁኔታ/የሕግ አግባብ/ እንጂ ያልተያዙ ሰዎች ከፍርድ በፊት በእስር ስለሚቆዩበት የሕግ አግባብ አይደለም። ይህም ሕግ አውጪው የዋስትና ገደቡ በተያዙ ሰዎች ላይ ብቻ እንዲወሰን ያደረገ መሆኑን ያጠናክርልናል።

1.6. ከዚህም በላይ፣ በዚሁ ድንጋጌ ስር "[....] በዋስትና መለቀቅ/መልቀቅ አይችልም።" የሚለዉ ሐረግም የሚያመለክተዉ አስቀድሞ የተያዘ ሰው መኖሩን እና ይህም የተያዘው ሰው በዋስ ስለሚለቀቅበትና ስለማይለቀቅበት ሕጋዊ ሁኔታ ነዉ። ምክንያቱም መልቀቅ/መለቀቅ የሚለው ቃል አስቀድሞ መያዝና መታሰርን ታሳቢ ያደርጋልና። በሌላ አነጋገርም፣ "በዋስትና መለቀቅ አይችልም" የሚለው ሐረግ  "ከእስር ነፃ መዉጣት/መፈታት" (Release from custody) የሚል ፅንሰ-ሀሳብ ያዘለ ነው። ይህም ጽንሰ ሃሳብ በድንጋጌው ስር ዋስትና የሚከለከለው ሰው ቀድሞ ሲል በአካል ተይዞ በቁጥጥር ስር የሚገኝ መሆኑን ያመለክታል። በአጠቃላይ የድንጋጌው ይዘት በግልጽ በዋስ "መለቀቅ" ላይ ያተኮረ ሲሆን በዋስ ለመለቀቅ ደግሞ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ እና በጸረ ሙስና ልዩ ሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ አዋጅ መሠረት አስቀድሞ በሚመለከተው ፖሊስ ወይም በፍርድ ቤት በኩል መያዝና መታሰርን ይጠይቃል።

መልቀቅ ምን ማለት እንደሆነ ከወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 72 ድንጋጌ መገንዘብ የሚቻል ሆኖ፣ በአዋጁ አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ ላይ "መለቀቅ/መልቀቅ" የሚለው ቃል ታሳቢ የሚያደርገው የቀደመ መያዝን ሲሆን መልቀቅ/መለቀቅ የሚለው የድንጋጌው ቃል የሚያመለክተው ከመለቀቁ በፊት የተያዘ ሰው ስለመኖሩና የተያዘውም ሰው በዋስ እንዲለቀቅ ሲወሰንለት ከተያዘበት የማረፍያ ቤት ለቆ የሚወጣ/ከእስር የሚፈታ መሆኑን ነው። በሌላ አነጋገርም፣ በድንጋጌዉ ላይ "በዋስትና መለቀቅ አይችልም።" የሚለዉ ሐረግ በሙስና ወንጀል አስቀድሞ መያዝና መታሰርን ታሳቢ ያደርጋል። በሙስና ወንጀል ተጠርጥሮ ያልተያዘ የተከሰሰ ሰዉ ወይም በሙስና ወንጀል ተጠርጥሮ ተይዞ በዋስትና ከተለቀቀ በኋላ የተከሰሰ ሰዉ "በዋስትና መለቀቅ" የሚለው ስሜት የሚሰጥ ምክንያታዊ የሆነ ትርጉም ስለማይሰጥ ወይም ትርጉም የለሽ ወለፈንዲ ስለሚያደርገው የአዋጁ አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ በሙስና ወንጀል ተጠርጥሮ ያልተያዘ ሆኖ በማናቸውም የሙስና ወንጀል የተከሰሰ ሰዉ ወይም በሙስና ወንጀል ተጠርጥሮ ተይዞ በዋስትና ከተለቀቀ በኋላ በማናቸውም የሙስና ወንጀል የተከሰሰ ሰዉ ላይ ተፈፃሚነት የለዉም። ይህም ማለት ድንጋጌው በተከሰሰበት ጊዜ በአካል ባልተያዘ በማናቸውም የሙስና ወንጀል በተከሰሰ ማንኛውም ሰዉ ላይ ተፈጻሚነት አይኖረውም ማለት ነው። በዚህ አግባብ ይህ ቃል(መለቀቅ) በቀጥታ አስቀድሞ አንድ ሰው "ተይዟል" የሚል እውነታ እንዳለ ያሳያል።

ከዚህም አንጻር ስንመረምረው፣ "መለቀቅ"/መልቀቅ የሚለው ግስ ከማንኛውም እስራት ወይም ቁጥጥር ነጻ መዉጣት/መፈታት ማለት ነው። በዚህም መሠረት ድንጋጌው ተፈጻሚነት ያለው በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕጉ ወይም/እና በልዩ ሥነ ሥርዓት ሕጉ መሠረት በአካል ለተያዙ ሰዎች ብቻ ነው። ምክንያቱም "በዋስትና መለቀቅ/መልቀቅ አይችልም" የሚለው ሐረግ እንደሚያመለክተው አስቀድሞ በሙስና ወንጀል የተያዘ ሰው በሌለበት ሁኔታ ዋስትና መፍቀድም ሆነ መከልከል ብሎ ነገር አይኖርም። የዋስትና መብትን ለማንሳት የሚችለው የመብቱ ተጠቃሚው በሙስና ወንጀል የተያዘው ሰው እንጂ ዐቃቤ ሕግ አይደለም።[4] ፍርድ ቤትም በሙስና ወንጀል የተያዘ ሰዉ በሌለበት ሁኔታ የዋስትና መብት ሊፈቀድ ይገባል ወይንስ አይገባም? የሚል ጭብጥ በመያዝ ወይም በማንሳት መመርመርና መወሰን አይገባውም፣ አይችልምም። ስለሆነም አንድ በሙስና ወንጀል የተከሰሰ ሰው በቁጥጥር ስር ሳይውል ወይም ሳይያዝ የሙስና ወንጀል ክስ እንደቀረበበት እንደሰማ በገዛ ፍቃደኛነት ከውጭ/ከቤቱ ወጥቶ ጉዳዩ የቀረበበት ፍርድ ቤት ዘንድ በቀረበ ጊዜ የአዋጁ አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ በእርሱ ላይ ተፈፃሚነት የለውም።

1.7. በወንጀል ሕግ አተረጓጎም መርሆች መሠረት ጥብቅ የሆነ የወንጀል ህግ አተረጓጎም መርህ (Nullum Crimen Sine Lege) ማንኛውም የዋስትና ክልከላ ወይም ገደብ በግልፅና የማያሻማ ሆኖ እንዲገለፅ እና በሕጉ ቃል ላይ በግልጽና በማያሻማ ሁኔታ ከተገለፀው ቃል በላይ ተለጥጦ በስፋት እንዲተረጎምና እንዲተገበር አይፈቅድም። እንዲሁም ዋስትና መከልከል መርሕ ሳይሆን ልዩ የሥነ ሥርዓት ሁኔታ(ድንጋጌ) በመሆኑ ጥብቅ የሆነ የወንጀል ህግ አተረጓጎም መርህ (Nullum Crimen Sine Lege) መሰረት በጠባቡ መተርጎም እንዳለበት ከግንዛቤ ማስገባት ይገባል፡፡ በተጨማሪም፣ ኢትዮጽያ ያጸደቀቻቸውን ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን (ለምሳሌ፣ ዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃልኪዳን አንቀጽ 9(3)[5]፣ የአፍሪካ ቻርተር አንቀጽ 6 እና ሁሉን አቀፍ  የሰብዓዊ መብቶች መግለጫን) ከግንዛቤ ባስገባና ኢትዮጵያ ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሕግጋት፣ ስምምነቶች፣ ሰነዶችና መርሆዎች ጋር በተጣጣመ መልኩ መተርጎም እንዳለባቸው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕገ መንግሥት አንቀጽ 13(2) ይደነግጋል፡፡ ኢትዮጵያ ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሕግጋት ድንጋጌዎች መረዳት የሚቻለው ዋስትና የማይፈቀድባቸውን ልዩ ሁኔታዎች በመደንገግ ረገድ ለሕግ አውጪው ሥልጣን የተሰጠው መሆኑን ነው፡፡ ነገር ግን ሕግ አውጪው የዋስትና መብትን በመገደብ የሚያወጣው ሕግ ከሕገ መንግሥቱና ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሕግጋት ጋር የተጣጣመ እና የዋስትና መብትን በውስን አድማስ ከመገደብ አልፎ ዋናውን መብት የሚያሳጣና የሚንድ መሆን እንደሌለበት ያስቀምጣል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ፣ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስት ውስጥ በወንጀል ጉዳይ ተጠርጥረው ፍርድ ቤት የሚቀርቡ ሰዎችን መብት ለማስከበር የሚረዱ ተለያዩ ድንጋጌዎች ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ ሕገ መንግስታዊ ድንጋጌዎች መካከል አንዱ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 17 ስር የተመለከተው ሲሆን በዚህ ድንጋጌ መሠረት አንድ ሰው በሕግ ከተደነገገው ስርዓት ውጪ ሊያዝ፣ ክስ ሳይቀርብበት ወይም ሳይፈረድበት ሊታሰር አይገባም፡፡ በሌላ በኩል፣ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 20(3) ላይ የተከሰሱ ሰዎች በፍርድ ሂደት ባሉበት ጊዜ እንደጥፋተኛ ያለመቆጠር መብት አላቸው፡፡ ዳኞች የዳኝነት ተግባራቸውን ነፃ ሆነው በሕግ ብቻ በመመራት መስራት እንዳለባቸው ደግሞ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 79(3) ስር ተመልክቷል፡፡ የሕግ የበላይነት ባለበት ሃገር የዳኞች የዳኝነት ሥልጣን በሕግ የተገደበ ነው፡፡ ይህም ማለት ዳኞች በሕግ ብቻ በመመራት መስራት ዉሳኔ ዳኝነት መስጠት ይጠበቅባቸዋል ማለት ነው፡፡ ስለዚህም በግልፅ በሕግ ዋስትና ከተከለከለባቸው ሁኔታዎች ውጪ ባሉ ሁኔታዎች ፍርድ ቤቶች ሰዎችን ከፍርድ በፊት በእስር እንዲቆዩ ማድረግ አይኖርባቸዉም፡፡ ስለሆነም ፍርድ ቤቶች አንድ ያልተያዘ የተከሰሰ ሰው ከፍርድ በፊት በእስር/በማረፍያ ቤት እንዲቆይ ትእዛዝ ከመስጠታቸው በፊት በቅድሚያ ያልተያዘ ሆኖ የተከሰሰው ሰው ባልተያዘበት ሁኔታ በግልጽ በሕግ ዋስትና የተከለከለ መሆኑ ወይም አለመሆኑን ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ በዚህም አግባብ በግልጽ በሕግ ካልተደነገገ በቀር ፍርድ ቤቶች ዋስትና መከልከል የለባቸውም፡፡ በመሆኑም የአዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 3(1) ስር የተመለከተዉ የዋስትና ክልከላ አንድ ሰው በተከሰሰበት ጊዜ በሙስና ወንጀል ያልተያዘ ከሆነ ተፈጻሚነት የለውም። ከዚህም አንጻር፣ የሙስና ወንጀል ተከሰሰዉ ሰዉ በቁጥጥር ስር ሳይውል ወይም ሳይያዝ የሙስና ወንጀል ክስ እንደቀረበበት እንደሰማ በራሱ ፍቃደኛነት ከውጭ ጉዳዩ የቀረበበት ፍርድ ቤት ዘንድ የቀረበ እንደሆነ የአዋጁ አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ በእርሱ ላይ ተፈፃሚነት የለውም።

1.8. የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 19(6)[6] የሚደነግገው በመርህ ደረጃ በዋስ የመፈታት/የመለቀቅ መብት የማንኛውም የተያዘ ሰው ሕገ መንግስታዊ የሆነ መብት መሆኑን ሲሆን ይህ የሕገ መንግስቱ ድንጋጌ በግልጽ የሚገልፀው በመርህ ደረጃ በዋስ የመፈታት/የመለቀቅ መብት ማንኛውም በወንጀል ተጠርጥሮ የተያዘ ሰው መብት ሲሆን በሕግ በተደነገጉ ልዩ ሁኔታዎች ግን ፍርድ ቤት በተያዙ ሰዎች የሚቀርብለትን በዋስትና የመለቀቅ ጥያቄ ሊነፍግ፣ ሊገድብ እንደሚችል ወይም በቂ የሆነ የዋስትና ማረጋገጫ አስቀርቦ የመፍቻ ትዕዛዝ ለመስጠት የሚችል መሆኑን ነው፡፡ ስለዚህም የዋስትና መብት በወንጀል ለተያዘ ሰዉ የተሰጠ ህገ-መንግስታዊ የሆነ መብት ስለመሆኑ በኢ.ፌ.ድ.ሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 19/6/ ላይ ተቀምጧል፡፡ በመሰረቱ የዋስትና መብት መርህ /Principle/ ስለሆነ እና አንድ በሙስና ወንጀል የተያዘ ሰው የዋስትና መብቱ ሊነፈግ የሚገባው በሕግ በተመለከተ በልዩ ሁኔታ (Exceptionally) ስለሆነ ልዩ ሁኔታው በጥንቃቄና በጠባቡ ነው መታየት አለባቸው፡፡ በመሆኑም በዋስ የመፈታት መብት ያለው ማንኛውም በወንጀል የተያዘ ሰው እንጂ በወንጀል ያልተያዘ ሰው አይደለም፡፡[7] እዚህ ላይ መጠቀስ ያለበት ነገር በሕገ መንግሥት አንቀጽ 19(6) ላይ የዋስትና መብት የተረጋገጠለት በማናቸውም ወንጀል ተጠርጥረው "ለተያዙ ሰዎች" ብቻ ነው። ይህም የሆነበት ምክንያት ያልተያዘ ሰው ባልተያዘበት ሁኔታ በዋስ ልለቀቅ ብሎ ዋስትና የሚጠይቅበት ነባራዊ ሁኔታ ባለመኖሩ ነው።

የዋስትና መብት በባሕሪው ከእስር/ከመታሰር ስለሚለቀቅበት ዘዴ የሚደነግግ ነዉ። የዋስትና ጽንሰ-ሀሳብ አስቀድሞ ከመያዝ ወይም ከመታሰር ጋር በጥብቅ የተቆራኘ መሆኑን ያሳያል። መያዝና እስራት ሳይኖር አንድ ሰው በዋስ “የሚለቀቅበት” ነገር አይኖርም። ዋስትና ከእስር ለመፈታት የሚያገለግል ዘዴ እንጂ የማሰሪያ ዘዴ አይደለም። እስር በሌለበት ሁኔታ፣ "በዋስ መልቀቅ" የሚለው ጽንሰ-ሀሳብ ራሱ ትርጉም አይሰጥም። የተያዘ ሰው በሌለበት ሁኔታ የዋስትና ድንጋጌን ማንሳት ራሱ ትርጉም የለውም። የፌዴራሉ ሕገ መንግስት አንቀጽ 19(6) ራሱ የዋስትና መብትን ከእስር ሁኔታ ጋር ያገናኛል። ይህም የሕገ መንግስታዊ ድንጋጌ የዋስትና ጥያቄዎች የሚነሱት ከመታሰር በኋላ ብቻ መሆኑን ሕገ መንግስታዊ መሠረት ያቋቁማል። በአጠቃላይ የዋስትና መብት በቀጥታ ከእስር ጋር በጥብቅ የተያያዘ ጉዳይ ነው። "በዋስትና መልቀቅ" የሚለው ጽንሰ-ሀሳብ ቀድሞ የነበረ እስር ወይም መቆጣጠር እንዳለ ይገልጻል። ስለዚህም ትክክለኛው ሂደት የሚከተለው መሆን አለበት፡- 1. መያዝ (Arrest) 2. የእስር ትእዛዝ (Detention Order) 3. የዋስትና ጉዳይ ግምገማ (Bail consideration) ነዉ። 

ነገር ግን የመያዝና የእስርትእዛዝ ደረጃዎችን በሙሉ አልፎ ያላግባብ በቀጥታ ዋስትና መከልከል  መሠረታዊ የሆኑ የወንጀል ክርክር አመራር መርሆችን የሚጣስ ነው። የዋስትና ገደቦች/ክልከላዎችን በሙስና ወንጀል ላልተያዘው ሰው እንደሚሰራ ትርጓሜ መስጠት የሚያመራው ወደ ተሳሳተ ውስብስብ ምክንያታዊ ያልሆነ ውጤት ነው፡ የዋስትና ድንጋጌን ማንኛውም በፈቃዱ የቀረበ የተከሰሰ ሰው ዋስትና እንዳይሰጠው ወደሚል የተሳሳተ ውጤት የሚያመራ ሲሆን ይህም ሕግ አውጭው አካል ያላሰበዉና ከሕገ መንግስቱ መርሆዎች ጋር የማይጣጣም ውጤት ነው። ከዚህም በመነሳት የአዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 3(1) መተግበር የሚኖርበት በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 19/6/ ስር የተረጋገጠውን የተያዙ ሰዎችን ሕገ መንግስታዊ የዋስትና መብት ባገናዘበ መልኩ ነው እንደዚውም የአዋጁ አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ የሕገ መንግስቱን አንቀጽ 9(1)-(2)፣ 9(4)፣ 13(1)-(2)፣ 17ና 20(3) ድንጋጌዎችን ባከበረ መልኩ መተርጎም አለበት[8] በዚህም አግባብ የአዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ ተፈፃሚ የሚሆነው በሙስና ወንጀል የተያዘ ሰው ከተያዘበት ሁኔታ በዋስ እንዲለቀቅ ማመልከቻ ለሚመለከተው ፍርድ ቤት ሲያቀርብ ነው።

ሆኖም ግን በአዋጅ ቁጥር 434/1997 አንቀጽ 58(2)[9] (59(2) እንደተሻሻለው) መሠረት ከዚህ አዋጅ ጋር የማይቃረኑ ማናቸውም ሌሎች ሕጎች በዚህ አዋጅ ውስጥ ባልተሸፈኑ ጉዳዮች ላይ ተፈጻሚነት ይኖራቸዋል። በዚህም መሠረት የወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 74 በሙስና ወንጀል የዋስትና ጉዳዮችም ላይ ተፈጻሚነት ያለው ሲሆን በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 74 ላይ እንደተመለከተዉ አዲስ ነገር (new facts) ሲከሰት የዋስትና ጉዳይ (Bail consideration) ሊከለስ ይችላል። ይህ ማለት የዋስትና ጉዳይ አንዴ ታይቶ ከተወሰነ በኃላ በቀጣይ ሂደት መልሶ ሊታይ የሚችለው ልዩ ሁኔታ ነዉ። ይኸዉም አዲስ ነገር (new facts) የተከሰተ ብቻ ነው። በዚህም መሠረት ልዩ ሁኔታ (አዲስ ነገር) ከተከሰተ፣ ዋስትና እንደገና ሊታይ ይችላል። ከዚህ ዉጭ የዋስትና ጉዳይ አንዴ ታይቶ ከተወሰነ በኃላ በቀጣይ ሂደት መልሶ ሊታይ አይችልም። ሲጠቃለል የዋስትና መብት የተያዘ ሰዉ ከተያዘ በኃላ የሚጠይቀዉና የሚወሰንለት ጉዳይ እንጂ በተያዘዉ ሰዉ ላይ የተጣለበት ግዴታ አይደለም:: በመሆኑም በመርህ ደረጃ የዋስትና መብት ከእስር ጋር የተያያዘ ነው። ሆኖም አዲስ ነገር (new facts) ሲከሰት የዋስትና ጉዳይ መልሶ ሊታይ ይችላል።

1.9. በአጠቃላይ የሕግ አውጪው ሀሳብ እንደተገለጸው ድንጋጌው በፖሊስ ወይም በፍርድ ቤት በተሰጠ የመያዥያ ትእዛዝ መሠረት አስቀድሞ በሙስና ወንጀል ተጠርጥሮ በአካል የተያዘ ሰዉን ብቻ ያካትታል። የአዋጁ አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ በሙስና ወንጀል ያልተያዘ ሰው ሳይሆን በሙስና ወንጀል የተያዘ ሰው በዋስ እንዲለቀቅ ለማመልከት ይችላል የሚል ሆኖ እያለ የስር ፍርድ ቤት በሙስና ወንጀል በአካል ባይያዝም እንኳ በሕግ/በአዋጁ አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ/ ዋስትና ተከልክሏል በማለት አቋም መያዙ ከአዋጁ አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ ይዘትና እሳቤ ጋር የሚጋጭ ነው፡፡ የዳኝነት አካል የአዋጅ አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ ተግባራዊ ትርጉም እንዲኖረው ያደርጉ ዘንድ ሕግ እንዲያወጡ ወይም ሕግ እንዲያሻሽሉ መፍቀድ አይኖርበትም፡፡ ከዚህም አንጻር፣ በሙስና ወንጀል ያልተያዘ ወይም ተይዞ በዋስትና ወጥቶ ሳይያዝ በሙስና ወንጀል ተከሶ ፍርድ ቤት የቀረበ ማናቸውም ሰው ከፍርድ በፊት በእስር እንዲቆይ ለሚሰጥ ውሳኔ የሕግ መሠረት መስጠት የሚቻለው ሕጉን በማሻሻል እንጂ ሕጉን ከደረቅ (ነጠላ) ግልጽ ንባቡ እንዲያፈነግጥ በማድረግ አይደለም፡፡

እንዲሁም በሕግ እንደሚታወቀው «ዳኞች ሕግ ነጋሪዎች እንጂ ሠሪዎች አይደሉም» (The role of the judge is to declare what the law is, not to make it እንዲል)፡፡[10] ዳኞች ሕግ የሚሠሩ ከሆነ፣ የሕጉን ይዘት ወሰንና ገደብ መተንበይ ካልሆነ በቀር በእርግጠኝነት ማወቅና መናገር አይቻልም፡፡ በተለይ ዳኞች ሕግ የሚያወጡ ከሆነ፣ በሕግ አውጭውና በዳኝነት አካሉ መካከልም ያለውን ሕገ መንግስታዊ የሆነ የሥልጣን ክፍፍል ይቃረናል፡፡ ከዚህም አንጻር፣ የአዋጁ አንቀጽ 3(1) ተፈጻሚ ሊደረግ የሚችለው አንድ በሙስና ወንጀል ጋር በተያያዘ በሕጋዊ መንገድ በአካል የተያዘ/በቁጥጥር ስር የወደቀ፣ በአዋጅ ቁጥር 434/1997 አንቀጽ 4(2) መሠረት በመርማሪው ፖሊስ በዋስትና ያልተለቀቀ፣ እና በአዋጁ አንቀጽ 3(1) ላይ እንደተመለከተው በሙስና ወንጀል ተጠርጥሮ በአካል የተያዘ ሰዉ በዋስ ከእስር እንዲለቀቅ/እንዲፈታ ለሚመለከተው ፍርድ ቤት የዋስትና ማመልከቻ ሲያቀርብ ብቻ ነው። በሙስና ወንጀል ያልተያዘ ሰው ላይ ግን ይህ ድንጋጌ ሊተገበርበት አይችልም። ይህም ሲባል "በሙስና ወንጀል የተያዘ ሰው" የሚለው ሐረግም ሆነ ሌሎችም የድንጋጌው ቃላቶችና ሐረጎች ግልጽና የማያሻሙ በመሆናቸው የድንጋጌው ይዘት ግልጽነት ያለው ስለሆነ የሕግ ትርጉም አያሻቸውም። በዚህም ምክንያት ግልጽ ይዘት ያለው ድንጋጌ ደግሞ ትርጉም ሳያስፈልገው በቀጥታ ተግባራዊ ሊሆን የሚገባው ነው። ስለዚህ በሙስና ወንጀል ተጠርጥሮ አግባብነት ባለው አካል ያልተያዘ የተከሰሰ ሰው በአዋጁ አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ ስር የዋስትና ክልከላ አይደረግበትም። ስለሆነም የአዋጁ አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ በሙስና ወንጀል በአካል የተያዙ እና ፍርድ ቤት ፊት የቀረቡ ሰዎችን ብቻ የሚመለከት ነዉ።

1.10. ሆኖም ግን ዐቃቤ ሕጎችን ጨምሮ አንዳንድ የሕግ ባለሙያዎች የሕግ አውጪው ትክክለኛ ሀሳብ የአዋጁ አንቀጽ 3(1) በሙስና ወንጀል የተያዙ ሰዎች ላይ ብቻ እንዲገደብ ሳይሆን በሙስና ወንጀል የተከሰሱ ሰዎችንም እንዲጨምር ነው በማለት ተቃራኒ የሕግ ሙግት ሊያነሱ ይችሉ ይሆናል። ይህም ሲባል አንዳንድ የሕግ ባለሙያዎች የሕግ አውጪው ሀሳብ አግባብ ባለው የሕግ አስከባሪ አካል በሙስና ወንጀል በአካል ባይያዝም/በቁጥጥር ስር ባይውልም እንኳን ከአሥር ዓመት በላይ በሆነ ጽኑ እስራት ሊያስቀጣ በሚችል የሙስና ወንጀል የተከሰሰውን ሰውም የዋስትና መብቱ እንዲከለከል ነው በማለት በበኩላቸው የመሰላቸውን የሕግ ክርክር ሊያነሱ ይችሉ ይሆናል። ይሁን እንጂ ይሁን እንጂ ይህ ተቃራኒ የመከራከሪያ ነጥብ በሚከተለው ምክንያት የሕግ ድጋፍ የለውም፡፡ ይኸውም:- የሕግ አውጪው ትክክለኛ ሃሳብ የሚገለጸው በሕግ ቋንቋ በመሆኑ የሕግ አውጪው ትክክለኛ ሃሳብ ቀዳሚና ዋና ገዢ የሆነ ምንጭ የሕጉ ቋንቋ/ቃላትና ሐረግ (Verba legis) ነው የሕግ አረዳድም ሆነ ትርጉም የሚጀመረውም ሆነ የሚደመደመውም በሕጉ ቋንቋ (Language/wording of the law) ላይ በመመስረት ነው። ሕጉ ግልጽና የማያሻማ እስከሆነ ድረስ ፍርድ ቤቶች ከሕጉ ቋንቋ/ቃላት በላይ መመልከት የለባቸውም። በሌላ አገላለጽ፣ ሕጉ ግልጽነት የጎደለውና አሻሚ ካልሆነ በስተቀር ፍርድ ቤቶች በሕጉ ቃላት ላይ ከመቆም ውጪ በዘፈቀደና በመሰለኝ መስራት አይኖርባቸውም። በዚህም መሠረት የአዋጁ አንቀጽ 3(1) ላይ የተገለጸው የሕግ አውጪው ቋንቋ ደግሞ ከላይ በጥቅስ ውስጥ የተቀመጠው ሲሆን የሕግ አውጪው ይፋዊ ትክክለኛ ሃሳብ በዋናነት የተገለጸውም ከዚህ በላይ በተመለከቱት የድንጋጌው ቃላትና ሐረጎች ውስጥ ነው።

የአዋጁ አንቀጽ 3(1) ላይ የተገለጹት "በሙስና ወንጀል የተያዘ ሰው"፣ "በዋስ እንዲለቀቅ" እና "በዋስትና መለቀቅ አይችልም" የሚሉት ቃላት ላይ እንደተመለከተው ድንጋጌው ከዋስትናው ጉዳይ በፊት የቀደመ መያዝን/መታሰርን ታሳቢ የሚያደርግ ሲሆን ይህም የሚያመለክተው የዋስትና ማመልከቻ ለፍርድ ቤት ከመቅረቡ በፊት እና/ወይም በቀረበበት ጊዜ በሙስና ወንጀል የተያዘ ሰው የሚኖር መሆኑን ነው። የሕጉ ቃላት ግልጽ መሆንና አሻሚ አለመሆን የሕግ አውጪ ሃሳብ ነው በሚል የሚቀርብ ማናቸውም ግምታዊ/ምናባዊ ሀሳብ (Hypothetical legislative intent)ን ውድቅ ያደርጋል። ስለዚህም የአዋጁ አንቀጽ 3(1) ላይ የተገለጹት "በሙስና ወንጀል የተያዘ ሰው"፣ "በዋስ እንዲለቀቅ" እና "በዋስትና መለቀቅ አይችልም" የሚሉት ቃላት እንደሚያመለክቱት አስቀድሞ በሙስና ወንጀል (ተጠርጥሮ) የተያዘ ሰው ሳይኖር የዋስትና ጉዳይ አይነሳም፣ በዋስትና መለቀቅ/መልቀቅ ወይም አለመለቀቅ/አለመልቀቅ የሚባል ነገርም የለም። ከዚህም ባለፈ፣ ዋስትና መከልከል መርሕ(Principle) ሳይሆን ልዩ ሁኔታ (An exception) በመሆኑ ጥብቅ የሆነ የወንጀል ህግ አተረጓጎም መርህ (Nullum Crimen Sine Lege) መሰረት የአዋጁ አንቀጽ 3(1) በጣም በጠባቡ መተርጎም አለበት፡፡ በመሆኑም ከአሥር ዓመት በላይ በሆነ ጽኑ እስራት ሊያስቀጣ በሚችል የሙስና ወንጀል እስከተከሰሱ ድረስ የአዋጁ አንቀጽ 3(1) በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ላልተያዙ የተከሰሱ ሰዎችም ጭምር ተፈጻሚነት አለው በማለት የሚቀርብ መከራከሪያ ሕጋዊ መሠረት ያለው አሳማኝ ክርክር መስሎ አይታየኝም።

በሌላ በኩል፣ በተሻሻለው የፀረ-ሙስና ልዩ የሥነ ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ አዋጅ ቁጥር 434/1997 መቅድም/መግቢያ (Preamble) ላይ አዋጁን ለማሻሻል ካስፈለጉበት ምክንያቶች አንዱ "በሙስና ወንጀል የተያዙ ወይም የተከሰሱ ሰዎች በዋስትና ስለሚለቀቁበት ሁኔታ ዝርዝር ድንጋጌ መደንገግ በማስፈለጉ" እንደሆነ የተቀመጠ በመሆኑ የአዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 3(1) በሙስና ወንጀል የተያዙም ሆነ የተከሰሱ ሰዎች ላይ ተፈጻሚነት አለው የሚል ተቃራኒ የሕግ ክርክር ሊያነሱ የሚችሉ አንዳንድ የሕግ ባለሙያዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ተቃራኒ ክርክር በሚከተሉት ምክንያቶች የሕግ መሠረት የለውም፡፡ ይኸውም:- አንደኛ፣ በአዋጁ መግቢያ (Preamble) ላይ "[….] የተከሰሱ ሰዎች በዋስትና ስለሚለቀቁበት ሁኔታ[….]" የሚለው አነጋገርም የዋስትና ጉዳይ ሊነሳ የሚችለው በሙስና ወንጀል የተያዘ ሰው ሲኖር ብቻ እንደሆነ ያመላክታል፡፡ ምክንያቱም በአዋጁ መግቢያ ላይ "ስለሚለቀቁበት ሁኔታ" የሚለው ሐረግ አስቀድሞ በሙስና ወንጀል የተያዘ/የታሰረ ሰው መኖሩን የሚያሳይ በመሆኑ ነው፤ አንድ ያልተያዘ ሰው ግን በዋስ ከእስር አይለቀቅም፡፡ ከእስር በዋስትና ለመለቀቅ አስቀድሞ መያዝን ይጠይቃል፡፡ ሁለተኛ፣ ከዚህ በላይ ከተቀመጠው የአዋጁ መግቢያ(Preamble) ይልቅ ዋናው/ዝርዝር ድንጋጌ የሆነው የአዋጁ አንቀጽ 3(1) የበላይና ቅድሚያ ተፈጻሚነት አለው፡፡ ከዚህ አንጻር፣ የአዋጁ አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ በሕግ ትርጉም እና ተፈጻሚነት ላይ ከመግቢያው በላይ ቅድሚያ ተፈጻሚነት ይኖረዋል፡፡ ሦስተኛ፣ የሕግ አውጪው ትክክለኛ ሃሳቡን በዝርዝር ድንጋጌ ላይ በግልጽ መደንገግ ያለበት ቢሆንም በአዋጁ አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ ላይ በሙስና ወንጀል የተያዘ ወይም የተከሰሰ ሰው በሚል በግልጽ ያልተቀመጠ ሲሆን የአዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 3(1) በሙስና ወንጀል የተያዘ ሰው ብቻ ዋስትና በግልጽ የሚገድብ ነው፡፡ ሕግ አውጪው በዝርዝር ድንጋጌው ውስጥ ሁለቱንም ለመሸፈን አስቦ ቢሆን ኖሮ በአዋጁ መግቢያ ላይ እንዳደረገው ሁሉ በሙስና ወንጀል የተያዘ ወይም የተከሰሰ ሰው በሚል በግልጽ ያስቀምጥ ነበር፡፡ ይህም ማለት ሕግ አውጪው የተከሰሱ ሰዎችንም እንዲጨምር በእርግጥ ቢፈልግ ኖሮ ይህንኑ በዝርዝር ድንጋጌው ላይ በግልጽ ያካትተው ነበር ማለት ነው፡፡

አራተኛ፣ የአዋጁ መግቢያ (Preamble) የሕጉን አጠቃላይ ዓላማ ብቻ ሲያሳይ፣ የሕጉ ድንጋጌዎች ግን በቀጥታ የሚተገበሩ የሕጉ አካል ሲሆኑ፣ የአዋጁ መግቢያ (Preamble) መረጃ ሰጪ ከመሆኑ አንጻር ሕጉ ግልጽ ባልሆነና አሻሚ በሆነ ጊዜ ለሕግ ትርጉም ግብዓትነት ከሚውል በቀር የሕግ አካል ባለመሆኑ በሕግ ተፈጻሚነትና አስገዳጅነት የለውም፡፡ ሆኖም የአዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ ግልጽና የማያሻማ በመሆኑ የሕግ ትርጉም አያስፈልገውም፡፡ ስለዚህም የአዋጁ መግቢያ በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ የተፈጻሚነት ስፋትና ወሰንና አስገዳጅነት ላይ ምንም ተጽዕኖ የለውም፡፡ አምስተኛ፣ በሕግ አንድን ነገር ወይም ሰው በግልጽ በመገለጽ ሌላውን ማግለል (Expressio unius est exclusion alterius) በሚለው የወንጀል ሕግ አተረጓጎም መርሕ መሰረት አንድ ሕግ የተወሰነ ነገር ወይም ሰውን ብቻ ከጠቀሰ፣ ያልተጠቀሱት ነገሮች አይጨመሩም፡፡ በዚህም መሠረት በአዋጁ አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ ላይ የአንዱ ምድብ (ማለትም በሙስና ወንጀል የተያዘ ሰው) በግልጽ መጠቀሱ ሌላኛው ምድብ (ማለትም በሙስና ወንጀል የተከሰሰ ሰው) ያልተካተተ መሆኑን ያመለክታል፡፡ ስድስተኛ፣ በተሻሻለው የፀረ-ሙስና ልዩ የሥነ ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ አዋጅ ቁጥር 434/1997 አንቀጽ 4(1)ም ሆነ ይህንኑ አዋጅ ለማሻሻል የወጣው የማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 3(1)ም ከሞላ ጎደል አንድ ዓይነት ሲሆኑ በእነዚህ በሁለቱም ድንጋጌዎች ላይ የተከሰሱ ሰዎች አልተካተቱም፡፡ ሰባተኛ፣ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 19(6) ላይ በግልጽ እንደተደነገገው በሕግ ገደብ የሚደረገው የተያዙ ሰዎች ባላቸው የዋስትና መብት ላይ ከመሆኑ አንጻር ባልተያዙ ሰዎች ላይ የዋስትና መብት ገደቦችን ማስቀመጥ/መደንገግ እንደጥፋተኛ ያለመቆጠር መብትን እና በጠቅላላው ሕገ መንግስታዊም ሆነ የሰብዓዊ መብት መርሆዎችን የሚጎዳ ብሎም የሚጥስ ይሆናል፡፡

በማጠቃለያ፣ ከዚህ በላይ የተጠቀሱት ምክንያቶች እንደሚያሳዩት የአዋጅ ቁጥር 434/1997 መግቢያ፣ የአዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 3(1) ላይ የተደነገገውን ግልጽና የማያሻማ የሆነ ዝርዝር ድንጋጌ አይሽረውም፡፡ በመሆኑም የአዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 3(1) ላይ የተመለከተው የዋስትና ገደብ ተፈጻሚነቱ በሙስና ወንጀል የተያዙ ሰዎች ላይ ብቻ እንጂ ያልተያዙ ሰዎች ላይ አይደለም፡፡

1.11. ለማጠቃለል ያህል፣ በአጠቃላይ በዋስትና የመፈታት መብት በወንጀል ተጠርጥረው ለተያዙ ሰዎች በሕገ መንግስቱ የተረጋገጠላቸው ሕገ መንግስታዊ የሆነ መብት ሲሆን በሕግ በግልፅ በተደነገገው በልዩ ሁኔታ መሰረት ካልሆነ በስተቀር በዋስ የመፈታት መብታቸው በዘፈቀደ ሊነፈግ የማይችል በመሆኑ የዳኝነት አካሉን ጨምሮ የሕግ አስከባሪ አካላት በሙሉ የዋስትና መብትን አክብረው የማስከበር ግዴታና ሃላፊነታቸውን በአግባቡና ወጥ በሆነ መንገድ ሊወጡ እና ዜጎችም ለዋስትና መብት መከበር የበኩላቸውን አስፈላጊውን ሁሉ ሊወጡ ይገባል፡፡ በተሻሻለው የፀረ-ሙስና ሥነ-ሥርዓትና ማስረጃ ህግ ማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 3(1) ላይ በሙስና ወንጀል የተያዘ ሰው በዋስትና እንዲለቀቅ ፍርድ ቤት ቀርቦ ለመጠየቅ ሕጋዊ መብት ያለው ቢሆንም የተከሰሰበት ወይም የተጠረጠረበት የሙስና ወንጀል ከአስር አመት በላይ በሆነ ጽኑ እስራት ሊያስቀጣ የሚችል ከሆነ ወይም ከአራት አመት በላይ እና ከአስር አመት በታች የሚያስቀጡ ተደራራቢ ወንጀሎች ሲኖሩ ተደምረው ከአስር አመት በላይ የሚያስቀጣ ከሆነ በዋስ እንደማይለቀቅ ተደንግጓል፡፡

ሆኖም ግን ድንጋጌው በግልጽ በሙስና ወንጀል ያልተያዙ ሰዎች በዋስትና ስለሚለቀቁበትና ስለማይለቀቁበት ሁኔታ አልደነገገም፡፡ ይልቅ ተጠቃሹ ድንጋጌ የሚገልጸው በሙስና ወንጀል የተያዘ ሰው በዋስ እንዲለቀቅ ለፍርድ ቤት ማመልከት የሚችል ስለመሆኑ፣ እና በዋስ እንዲለቀቅ ለፍርድ ቤት ያመለከተው በሙስና ወንጀል የተያዘው ሰው የተከሰሰበት ወይም የተጠረጠረበት የሙስና ወንጀል ከአሥር ዓመት በላይ በሆነ ጽኑ እስራት ሊያስቀጣ የሚችል ከሆነ ግን በዋስትና ከእስር ሊለቀቅ/ሊፈታ የማይችል ስለመሆኑ ነው። በመሆኑም በተሻሻለው የጸረ-ሙስና ሥነ-ሥርዓትና ማስረጃ ህግ ማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ በተለያዩ ምክንያቶች በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ከጅምሩ ያልተያዙ ሰዎች እና በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 74 ስር በተመለከተው መሠረት ካልሆነ በስተቀር በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ተይዘው በፖሊስ ወይም በፍርድ ቤት ዋስትና ከእስር ከተለቀቁ በኋላ በዚያው በተለቀቁበት ጉዳይ ላይ በሙስና ወንጀል የተከሰሱ ሰዎች ላይ ተፈጻሚነት የለውም፡፡

2.  የተያዘው ሰው የተከሰሰበት ወይም የተጠረጠረበት የሙስና ወንጀል ከአሥር ዓመት በላይ በሆነ ጽኑ እስራት ሊያስቀጣ የሚችል መሆን ወይንም አለመሆኑ ስለሚወሰንበት የሕግ አግባብ በተመለከተ፣

 

በዚህ ክፍል ስር ለዋስትና ክርክር አወሳሰን ዓላማ የተያዘው ሰው የተከሰሰበት ወይም የተተረጠረበት የሙስና ወንጀል ከአሥር ዓመት በላይ በሆነ ጽኑ እስራት ሊያስቀጣ የሚችል መሆን አለመሆኑ ስለሚወሰንበት የሕግ አግባብ ለመመልከት የምንሞክር ሲሆን ይኸውም:-

2.1. የአዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ ለብቻው ሲታይ በሙስና ወንጀል የተያዘው ሰው ዋስትና ሊከለከል የሚችለው የተከሰሰበት የሙስና ወንጀል ከአሥር ዓመት በላይ በሆነ ጽኑ እስራት ሊያስቀጣ የሚችል ከሆነ ብቻ ነው የሚል ግልጽ ይዘት ያለው ድንጋጌ በመሆኑ ትርጉም ሳያስፈልገው በቀጥታ ተግባራዊ ሊሆን የሚገባው ነው።

2.2. የፌደራል ሰበር ሰሚ ችሎትም በሰ/መ/ቁ 182050 ስር በሰጠው የሕግ ትርጉም[11] ላይ በተሻሻለው የፀረ ሙስና ጉዳዬች ስነ ስርዓት አዋጅ ቁጥር 882/07 አንቀፅ 3(1) መሰረት "ከአራት አመት በላይ እና ከአስር አመት በታች የሚያስቀጡ ተደራራቢ የሙስና ወንጀሎች ሲኖሩም እየተደመሩ ከ10 ዓመት በላይ የሚያስቀጣ ከሆነ ዋስትናን ያስከለክላል" የሚለው ሐረግ መሠረት ለተደራራቢ የሙስና ወንጀሎቹ ዋስትና ጥያቄን ለመወሰን ሊታይ የሚገባው መነሻ ቅጣታቸው ከአራት አመት በላይ የሆኑትን በመደመር ነው እንጂ መነሻው ከአራት አመት በታች ሆኖ ጣራው ከአራት በላይ ፅኑ እስራት የተቀመጡ ተደራራቢ ወንጀሎች ተደምረው ከ10 ዓመት ቢበልጥም ዋስትናን ለማስከልከል በቂ አይደለም በማለት ትርጉም ሰጥቶበታል። ከዚህም ትርጉም በመነሳት በእኩልነት መርህ መሠረት በተመሳሳይ "ከአስር ዓመት በላይ በሆነ ጽኑ እስራት ሊያስቀጣ የሚችል ከሆነ" የሚለው የድንጋጌው ሐረግም መተርጎም የሚገባው የዋስትና ጥያቄን ለመወሰን ሊታይ የሚገባው የመነሻ ቅጣትን እንጂ የቅጣት ጣሪያን አይደለም በሚል መሆን ይገባል።

2.3. ከዚህ አንጻር፣ የተያዘው ሰው ዋስትና ሊከለከል የሚችለው የተከሰሰበት ወይም የተጠረጠረበት የሙስና ወንጀል ከአሥር ዓመት በላይ በሆነ ጽኑ እስራት ሊያስቀጣ የሚችል መሆን አለመሆኑን ለዋስትና ዓላማ በወንጀል ሕጉ እና በቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 2/2006 ላይ የተመለከተውን መሠረት በማድረግ ሊተረጎም አይገባም፡፡ በመሆኑም የተሻሻለው የጸረ ሙስና ልዩ የሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ አዋጅን ለማሻሻል የወጣው አዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 2(3) ድንጋጌ ስር የተመለከተው "ከአስር ዓመት በላይ በሆነ ጽኑ እስራት ሊያስቀጣ የሚችል ከሆነ" የሚለው የሕጉ ሐረግ መታየት ያለበት ጣሪያው ሳይሆን መነሻ ቅጣቱ ነው፡፡ ይህም የሕግ አተረጓጎም በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 14፣ 17(1)-(2)፣ 19(3)(6)፣ 20(3) እና 22 ድንጋጌዎች ስር የተረጋገጡትን ሕገ መንግስታዊ የሆኑ መሠረታዊ መብቶችና ነጻነቶች መልኩ መሠረት ያደረገ ትርጉም ነው፡፡

እንደዚውም ይህም ትርጓሜ ልዩ ሁኔታ ደግሞ በጣም በጠባቡ መተርጎምና መተግበር አለበት የሚለውን የሕግ አተረጋጎም መርሕ መሠረት ያደረገ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ድንጋጌው በጠባቡ ሲተረጎም ለዋስትና ክርክር ውሳኔ አሰጣጥ ሲባል የተያዘው ሰው የተከሰሰበት ወይም የተጠረጠረበት የሙስና ወንጀል ከአሥር ዓመት በላይ በሆነ ጽኑ እስራት ሊያስቀጣ የሚችል መሆን አለመሆኑን የሚወሰነው የቅጣቱን ጣሪያ መሠረት በማድረግ ሳይሆን መነሻ ቅጣቱን መሠረት በማድረግ ነው፡፡ በተጨማሪም፣ ከፍርድ በፊት ያለመታሰር መብት ሕገ መንግስታዊ የሆነ መርሕ በመሆኑ፣ እና በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 19/6/ም ሆነ ሃገሪቱ ባጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶችም መሠረት ዋስትና መከልከል ልዩ ሁኔታ በመሆኑ፣ ልዩ ሁኔታ የደነገገው የአዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ በጣም በጠባቡ መተርጎም አለበት፡፡

2.4. ከዚህ በመነሳትም በሙስና ወንጀል የተያዘው ሰው የተጠረጠረበት ወይም የተከሰሰበት የሙስና ወንጀል ድንጋጌ መነሻ የጽኑ እስራት ቅጣት አሥር ዓመት በታችና ጣሪያው ደግሞ አሥር ዓመት በላይ በሆነ ጊዜ በአዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ አንቀጽ 3(1) ስር በተመለከተዉ መሠረት ዋስትና ለመከልከል የሚወሰደነው የድንጋጌው መነሻ የጽኑ እስራት ቅጣትን ወይንስ የጽኑ እስራት ቅጣት ጣሪያውን መሆን አለመሆኑን በተመለከተ፣ አንድ በሙስና ወንጀል የተያዘው ሰው የተጠረጠረበት ወይም የተከሰሰበት ወንጀል መፈጸሙ በዐቃቤ ሕግ ማስረጃ በፍርድ ቤት ቢረጋገጥና ሰውየውም በማስተባበል መከላከል አለመቻሉ ተረጋግጦ ጥፋተኛ ቢባል ሊቀጣ የሚችለው በሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 881/2007 ስር በተከሰሰበት የወንጀል ድንጋጌ ስር በተቀመጠው ቅጣት እና ቅጣትን ለመወሰን፣ የቅጣት አወሳሰንን ትክክለኛነትና አንድ ወጥነት ለማረጋገጥ ሲባል የወጣው የተሻሻለው የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 2/2006 መሠረት የወንጀሉን ደረጃና የእስራት ቅጣት መነሻ እርከን በማውጣት በሚወሰነው ነው፡፡

ይሁን እንጂ ለዋስትና ክርክር አወሳሰን ዓላማ የሚወሰደነው የድንጋጌው መነሻ የጽኑ እስራት ቅጣትን ወይንስ የጽኑ እስራት ቅጣት ጣሪያውን መሆን አለመሆኑን በሚመለከት በድንጋጌው ስር "[....] ከአሥር ዓመት በላይ በሆነ ጽኑ እስራት ሊያስቀጣ የሚችል ከሆነ" የሚለው ሐረግ ላይ እንደተመለከተው የአዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ ተፈጻሚ የሚሆነው የተያዘው ሰው የተከሰሰበት ወንጀል ጣሪያ ከአስር ዓመት በላይ ሊያስቀጣ የሚችል ከሆነ ብቻ ነው፡፡ የአዋጁ አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ ለብቻው ሲታይ በሙስና ወንጀል የተያዘው ሰው ዋስትና ሊከለከል የሚችለው የተጠረጠረበት ወይም የተከሰሰበት የሙስና ወንጀል ከአሥር ዓመት በላይ በሆነ ጽኑ እስራት ሊያስቀጣ የሚችል ከሆነ ብቻ ነው የሚል ግልጽ ይዘት ያለው ድንጋጌ በመሆኑ የሕግ ትርጉም ሳያስፈልገው በቀጥታ ተግባራዊ ሊሆን የሚገባው ድንጋጌ ነው። በመሆኑም ይግባኝ ባይ የተከሰሰበት የወንጀል ድንጋጌ መነሻ የጽኑ እስራት ቅጣት አሥር ዓመት በታች በመሆኑአዋጁ አንቀጽ 3(1) መሠረት በሕግ ዋስትና ተከልክሏል ሊባል አይችልም።

2.5. ሆኖም ምናልባት ይህ ድንጋጌ የህግ ትርጉም የሚሻው የተያዘው ሰው የተከሰሰበት የሙስና ወንጀል የሚያስቀጣው ጽኑ እስራት መነሻ ቅጣት ከአሥር ዓመት በታች ሆኖ የጽኑ እስራት ጣሪያው ከከአሥር ዓመት በላይ በሆነ ጊዜ ነው። በአዋጁ አንቀጽ 3(1) ስር "ከአስር ዓመት በላይ በሆነ ጽኑ እስራት ሊያስቀጣ የሚችል ከሆነ" የሚለው ሐረግ መታየት ያለበት ተከሳሹ በተከሰሰበት የወንጀል ድንጋጌ ላይ ከተመለከተው መነሻ ቅጣቱ ወይንስ ጣሪያው ነው ወይ? የሚለው ጭብጥ የሕግ ትርጉም ያሻዋል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ባጋጠመ ጊዜ የአዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ የተያዙ ሰዎችን ሕገ መንግስታዊ መብቶችን ባገናዘበ መልኩ ነው። በዚህም መሠረት ዋስትና ጉዳይ አዋሳሰን ሲባል የሚወሰደነው የድንጋጌው መነሻ የጽኑ እስራት ቅጣትን ወይንስ የጽኑ እስራት ቅጣት ጣሪያውን መሆን አለመሆኑን አሻሚነት ያለው ነው የሚባልም ከሆነ፣ በወንጀል ሕግ አተረጓጎም መርሆች አግባብ በጥብቅ የአተረጓጎም መርሕ መሠረት መተርጎም ያስፈልጋል፡፡

2.6. በዚህም መሠረት የተያዘው ሰው የተከሰሰበት የሙስና ወንጀል የሚያስቀጣው ጽኑ እስራት መነሻ ቅጣት ከአሥር ዓመት በታች ሆኖ የጽኑ እስራት የቅጣት ጣሪያው ከከአሥር ዓመት በላይ በሆነ ጊዜ የአዋጁ አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ ተፈጻሚነት አለው ወይንስ የለውም? ካለውስ እንዴት ይፈጸማል? የሚለውን ጉዳይ በሚመለከት ደግሞ:- የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰበር መዝገብ ቁጥር 231732[12] ስር ሐምሌ 27 ቀን 2015 ዓ.ም ከሰጠው ከሰጠው ገዢ የሆነ የሕግ ትርጉም አንጸር፣ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ቁ. 179416[13] ላይ ሰኔ 23 ቀን 2012 ዓ.ም ከሰጠው አስገዳጅ የህግ ትርጉም አንጸር፣ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 25[14] ስር ከተደነገገው የእኩልነት መርህ አንጸር፣ እና ዋስትና መከልከል መርሕ ሳይሆን ልዩ የሥነ ሥርዓት ሁኔታ(ድንጋጌ) በመሆኑ በጠባቡ መተርጎም ያለበት ከመሆኑ አንጻር፣ በሙስና ወንጀል ተጠርጥሮ የተያዘው ሰው ዋስትና ሊከለከል የሚችለው የተጠሪጠረበት ወይም የተከሰሰበት የሙስና ወንጀል "ከአሥር ዓመት በላይ በሆነ ጽኑ እስራት ሊያስቀጣ የሚችል" መሆን አለመሆኑን ለዋስትና ዓላማ መወሰን የሚገባው የተያዘው ሰው የተከሰሰበት ወይም የተጠረጠረበት የሙስና ወንጀል ድንጋጌ ስር የተቀመጠውን የቅጣት ክልልን(Sentencing range)፣ እና ቅጣትን ለመወሰን፣ የቅጣት አወሳሰንን ትክክለኛነትና አንድ ወጥነት ለማረጋገጥ ሲባል የወጣው በቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 2/2006 መሠረት የወንጀሉን ደረጃና የእስራት ቅጣት የመነሻ እርከን በማውጣት ሊቀጣ የሚችልበትን የቅጣት መጠን እግምት በማስገባት መሆን ይኖርበታል፡፡ ይህንንም አማራጭ መከራከሪያ የሚያጠናክረው ቅጣት የእያንዳንዱን ግለሰብ ግላዊ ሁኔታዎች ጭምር ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የሚወሰን መሆኑ ነው፡፡

በተለይም በድንጋጌው የሚለው የተያዘው ሰው "የተከሰሰበት ወይም የተጠሪጠረበት ወንጀል ድንጋጌ" ሳይሆን "የተከሰሰበት ወይም የተጠሪጠረበት የሙስና ወንጀል" የሚል ከመሆኑ አንጻር፣ እና ድንጋጌው ላይ "ሊያስቀጣ የሚችል ከሆነ" የሚል ከመሆኑ አንጻር፣ ለዋስትና ክርክር ውሳኔ አሰጣጥም ቢሆን አንድ ሰው "የተከሰሰበት ወይም የተጠሪጠረበት የሙስና ወንጀል" ከ10 ዓመት በላይ ሊያስቀጣ የሚችል መሆን አለመሆኑ የሚወሰነው በተከሰሰበት ወይም በተጠሪጠረበት የሙስና ወንጀል ድንጋጌ ላይ የተቀመጠውን የጽኑ እስራት ቅጣት ክልል (Sentencing range) በመመልከት ብቻ ሳይሆን ቅጣትን ለመወሰን፣ የቅጣት አወሳሰንን ትክክለኛነትና አንድ ወጥነት ለማረጋገጥ ሲባል የወጣው በቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 2/2006 መሠረት የወንጀሉን ደረጃና እርከን በመመርመር እና የተከሳሹን ግላዊ ሁኔታዎችን መነሻ በማድረግ በወንጀል ሕጉ ስር የተመለከቱትን ጠቅላላና ልዩ የቅጣት ማቅለያ ሁኔታዎችን እግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ጭምር ነው፡፡

ይሁን እንጂ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰበር መዝገብ ቁጥር 63344[15] ቅጽ 12 ላይ ፍርድ ቤቶች በሙስና ወንጀል የተያዘው ሰው የተጠረጠረበት ወይም የተከሰሰበት የሙስና ወንጀል ድንጋጌ ቅጣት ጣሪያን መሠረት በማድረግ ውሳኔ ሊሰጡ እንደሚገባ አስገዳጅ የሆነ የሕግ ትርጉም ሰጥቶበታል፡፡ ሆኖም ግን ኋላ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ቁ 182050 ላይ በተሻሻለው የፀረ ሙስና ጉዳዬች ስነ ስርዓት ማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 3(1) መሰረት "ከአራት አመት በላይ እና ከአስር አመት በታች የሚያስቀጡ ተደራራቢ የሙስና ወንጀሎች ሲኖሩም እየተደመሩ ከ10 ዓመት በላይ የሚያስቀጣ ከሆነ ዋስትናን ያስከለክላል" የሚለው ሐረግ መሠረት ለተደራራቢ የሙስና ወንጀሎቹ ዋስትና ጥያቄን ለመወሰን ሊታይ የሚገባው መነሻ ቅጣታቸው ከአራት አመት በላይ የሆኑትን በመደመር ነው እንጂ መነሻው ከአራት አመት በታች ሆኖ ጣራው ከአራት በላይ ፅኑ እስራት የተቀመጡ ተደራራቢ ወንጀሎች ተደምረው ከ10 ዓመት ቢበልጥም ዋስትናን ለማስከልከል በቂ አይደለም በማለት ትርጉም ሰጥቶበታል።

3.  መደምደሚያ

ፍርድ ቤቶች የሕጉን ግልጽ ቋንቋ/ቃላት በማይቃረን መልኩ መተግበር አለባቸው፡፡ ሕጉ ግልጽ ከሆነ፣ ከሕጉ ቃላት በላይ ማስፋት የለባቸውም፡፡ የተሻሻለው የጸረ ሙስና ልዩ የሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ አዋጅን ለማሻሻል የወጣው አዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ ተፈጻሚነት ያለው በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በተያዙ ሰዎች ላይ ብቻ ነው፡፡ ሕጉ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በተያዙ ሰዎች ላይ የዋስትና ክልከላ ማድረግ የሕጉ አቋም አይደለም፡፡ ፍርድ ቤቶች በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ያልተያዙ ሰዎች ወይም ከአሥር ዓመት በላይ ሊያስቀጣ በሚችል ያልተያዙ ሆነው በሙስና ወንጀል የተከሰሱ ሰዎች ላይ ድንጋጌውን ተፈጻሚ ለማድረግ የሚያስችላቸው ምንም የሕግ መሠረት የለም፡፡ በሌላ በኩል፣ ለዋስትና ክርክር ውሳኔ አሰጣጥ ሲባል አዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ መሠረት የሚወሰደው የቅጣቱ ጣሪያ ሳይሆን መነሻ ቅጣቱ ነው፡፡

 



[1] . ሙልጌታ በላይ፣ ያለ ፈጣን የፍርድ ሂደት ዋስትና የሚያስከለክል የወንጀል ድንጋጌ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 20 የሚፃረር ተግባርስለመሆኑ፣ሴፕቴምበር18,2024https://abyssinialaw.com/blog/20?tmpl=component&print=1&format=print(https://www.Abyssinialaw.com)

 

[2] . የተሻሻለው የጸረ-ሙስና ልዩ የሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ የወጣ አዋጅ ቁጥር 434/1997 አንቀጽ 4(1) እንዲህ ይላል:- "በሙስና ወንጀል የተያዘ ሰው በዋስ እንዲለቀቅ ለፍርድ ቤት ማመልከት ይችላል ሆኖም የተከሰሰበት ወንጀል ከአስር ዓመት በላይ ሊያስቀጣ የሚችል ከሆነ በዋስትና መልቀቅ አይችልምእንደዚውም የተሻሻለው የጸረ-ሙስና ልዩ የሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ አዋጅን ለማሻሻል የወጣ አዋጅ ቁጥር 239/1993 አንቀጽ 2(2) ላይ "በሙስና ወንጀል ተጠርጥሮ የተያዘ ሰው የዋስትና መብት አይኖረውም።" በሚል ተደንግጓል

[3] . የተሻሻለው የጸረ-ሙስና ልዩ የሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ የወጣ አዋጅ ቁጥር 434/1997 አንቀጽ 4(1) ድንጋጌ ላይ የተቀመጠው ድርብ ነጠላ ሰረዝ ሳይሆን አራት ነጥብ(።) ነው

[4] . በወንጀል ሥነ ሥርአት ህግ ቁጥር 28፣ 59ና ከቁጥር 63-79 ድረስ በተመለከቱት መሰረት በዋስ የመለቀቅ መብት ያላቸው በወንጀል የተያዙ ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡

[5] . ዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት አንቀጽ 9(3): "Anyone arrested or detained on a criminal charge shall be brought promptly before a judge or other officer authorized by law to exercise judicial power and shall be entitled to trial within a reasonable time or to release. It shall not be the general rule that persons awaiting trial shall be detained in custody, but release may be subject to guarantees to appear for trial, at any other stage of the judicial proceedings, and, should occasion arise, for execution of the judgment."

 

[6] . የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕገ መንግሥት አንቀጽ 19(6) እንዲህ ይላል፦ "የተያዙ ሰዎች በዋስ የመፈታት መብት አላቸው። ሆኖም በሕግ በተደነገጉ ልዩ ሁኔታዎች ፍርድ ቤት ዋስትና ላለመቀበል ወይም በገደብ መፍታትን ጨምሮ በቂ ዋስትና ማረጋገጫ እንዲያቀርቡ ለማዘዝ ይችላል፡፡

[7] . የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ሰ/መ/ቁ. 131863 ቅጽ 20 ሕዳር 08/2009 . የሕገ መንግስቱን አንቀጽ 19/6/ና 25ን መሠረት በማድረግ በሰጠው ፍርድ ላይ በወንጀል ተጠርጥሮ በህግ ከለላ/ጥላ ስር የሚገኝ ተጠርጣሪ በዋስትና የመለቀቅ ጥያቄ ባነሳ ጊዜ ተጠርጣሪው በከተማው ውስጥ ቋሚ የመኖርያ/የመታወቅያ ኣድራሻ የለውም በማለት የዋስትና መብቱን መከልከል ህገ መንግስታዊ ስላለመሆኑ፣ የሕግ ትርጉም ሰጥቶበታልበዚህም ትርጉም መሠረት በዋስትና የመለቀቅ ጥያቄ ለማንሳት መብት ያለው በወንጀል ተጠርጥሮ በህግ ከለላ/ጥላ ስር የሚገኝ ሰው እንደሆነ ተመልክቷል

[8] . በUDHR Article 9; ICCPR Articles 9, 10, 7; UN Human Rights Commitee Comment 8”; ሕገ መንግሥት 13(1), 17-19; 9, 10 መሠረት "ማንኛውም ሰው ከዘፈቀዳዊ መያዝ እና ታስሮ መቆየት (arbitrary arrest or detention) የመጠበቅ መብት አለው:: በ UN Human Rights Commitee ትርጉምም:- "Arbitrariness is not to be equated with “against the law”, but must be interpreted more broadly to include elements of inappropriateness, injustice, lack of predictability, and due process of law.” This means that arrest or remand in custody must be lawful, just, reasonable, necessary, predictable, and duly processed in all circumstances.”

[9] . የተሻሻለው የጸረ-ሙስና ልዩ የሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ የወጣ አዋጅ ቁጥር 434/1997 አንቀጽ 58(2) እንዲህ ይላል:- "ከዚህ አዋጅ ጋር የሚቃረኑ ማናቸውም ሌሎች ሕጎች በዚህ አዋጅ ውስጥ በተሸፈኑ ጉዳዮች ላይ ተፈጻሚነት አይኖራቸውም።"

[10] . የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕገ መንግሥት አንቀጽ 79(3) እንዲህ ይላል፦ "ዳኞች የዳኝነት ተግባራቸውን በሙሉ ነጻነት ያከናውናሉ። ከሕግ በስተቀር በሌላ አይመሩም።"

[11] . የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰበር መዝገብ ቁጥር 182050 ቅጽ 24 ታህሳስ 24 ቀን 2012 .ም የተሻሻለውን የፀረ-ሙስና ልዩ የስነ ስርአትና የማስረጃ ህግ (ማሻሻያ) አዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 3/1/ን መሠረት በማድረግ በሰጠው ፍርድ ላይ በሙስና ወንጀልች አዋጅ መሰረት በተመሰረት ክስ ተከሳሹ እንዲከላከል ብይን ተሰጥቶ ይህ ብይን የተሰጠበት ድንጋጌ አማራጭ ቅጣትን ያስቀመጠ ሆኖ በተሻሻለው የፀረ-ሙስና ልዩ የስነ ስርአትና የማስረጃ ህግ (ማሻሻያ) አዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 3/1 ሁለተኛ ሀሳብ ላይ ከአራት አመት በላይ በሚል የተደነገገውን ቅጣት እንደ መነሻ ቅጣት በመውሰድ የቅጣት መነሻቸው አራት ዓመት የሆነ በጽኑ እሥራት የሚያስቀጡ ወንጀሎችን የሚመለከት እንደሆነ አድርጎ በመውሰድ ዋስትናን መፍቀድ ተቀባይነት የሌለው ስለመሆኑ ወስኗል፡፡

 

[12] . የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰበር መዝገብ ቁጥር 231732 ስር ሐምሌ 27 ቀን 2015 ዓ.ም በሰጠው ፍርድ ላይ የወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 161(2)(ሀ) ድንጋጌ መሰረት አንድን የወንጀል ክስ ተከሳሽ በሌለበት ማየት የሚቻለው የቅጣቱ መድረሻ ከ12 ዓመት በላይ ስለሆነ ብቻ ሳይሆን መነሻውም ከ12 ዓመት በላይ መሆን እንዳለበት ገዢ የሆነ የሕግ ትርጉም ሰጥቶበታል።

[13]. የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰበር መዝገብ ቁጥር 231732 ስር ሐምሌ 27 ቀን 2015 ዓ.ም በሰጠው ፍርድ ላይ የወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 161(2)(ሀ) ድንጋጌ መሰረት አንድን የወንጀል ክስ ተከሳሽ በሌለበት ማየት የሚቻለው የቅጣቱ መድረሻ ከ12 ዓመት በላይ ስለሆነ ብቻ ሳይሆን መነሻውም ከ12 ዓመት በላይ መሆን እንዳለበት ገዢ የሆነ የሕግ ትርጉም ሰጥቶበታል።

[14]. የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕገ መንግሥት አንቀጽ 25 "ሁሉም ሰው በሕግ ፊት እኩል ናቸው፣ በመካከላቸውም ማንኛውም ዓይነት ልዩነት ሳይደረግ እኩል የሕግ ጥበቃ ይደረግላቸዋል፡፡ [….]" ይላል፡፡

[15]. የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰበር መዝገብ ቁጥር 63344 ቅጽ 12 ሐምሌ 28 ቀን 2003 .ም የአዋጅ ቁጥር 434/1997 አንቀጽ 4(1)ን መሠረት በማድረግ በሰጠው ፍርድ ላይ ፍርድ ቤቶች ተከሳሹ በቀረበበት የሙስና ወንጀል ክስ ጥፋተኛ ሆኖ ቢገኝ ሊጣልበት የሚችለውን የቅጣት ጣሪያ መነሻ በማድረግ ውሣኔ ሊሰጡበት የሚገባ ስለመሆኑ፣ እና ተከሳሹ የተከሰሰበት ወንጀል 10 ዓመት በላይ በእስራት ሊያስቀጣ የሚችል በሆነ ጊዜ በዋስትና ወረቀት እንዲለቀቅ ሊፈቀድ የማይችል ስለመሆኑ፣ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል፡፡

                                                                                                                                                               

Comments