Skip to main content

በአዲሱ የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር 1341/2016 የተካተቱ፣ በቀድሞው የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር 285/1994 ላይ የተደረጉ ለውጦች (The new Ethiopian VAT proclamation no. 1341/2024)


በአዲሱ የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር 1341/2016 የተካተቱ፣ በቀድሞው የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር 285/1994 ላይ የተደረጉ ለውጦች  (The new Ethiopian VAT proclamation no. 1341/2024)

ዝግጅት:- ሀብታሙ ጥላሁን (የህግ አማካሪና ጠበቃ)

  1. መግቢያ

የተጨማሪ እሴት ታክስ በዕቃ ወይም በአገልግሎት ፍጆታ ላይ የሚጣል ታክስ ሲሆን፤ በግብዓት ጥሬ ዕቃ (in put tax) ላይ የተከፈለን ታክስ በውጤት በምርት (out put tax) ላይ ከተሰበሰበ ታክስ በማቀናነስ ታክስ በታክስ ላይ እንዳይሰበሰብ (non-duble taxation) ማድረግ የሚያስችል ታክስ ነው፡፡ የተጨማሪ እሴት ታክስ በሽያጭ ደረሰኝ ላይ የተመሠረተ ዘመናዊ የታክስ ሥርዓት በመሆኑ ታክስ ከፋዮች የማቀናነሱ ሥርዓት ተጠቃሚ ለመሆን ደረሰኝ ሊኖራቸው ስለሚገባ ደረሰኝ በመጠየቅ አንዱ ሌላውን እንዲቆጣጠሩ ተደርጎ የተቀረፀ ለታክስ አስተዳደር አመቺ የሆነ የታክስ ዓይነት ነው፡፡

ከዚህም በላይ የተጨማሪ እሴት ታክስ በፍጆታ ላይ የተጣለ በመሆኑ፤ ፍጃታን በመቀነስ፣ ቁጠባን የሚያበረታታ የታክስ ዓይነት ሲሆን፤ በካፒታል ዕቃዎች ላይ ተፈፃሚ ስለማይሆን ኢንቬስትመንትን የሚያበረታታ የታክስ አይነት ነው፡፡

በእነዚህ እና በሌሎችም ምክንያቶች በዓለማችን ከ170 በላይ የሆኑ አገሮች የተጨማሪ እሴት ታክስን ሥራ ላይ አውለዋል። ይህም በመሆኑ ኢንቬስተሮች ሀብታቸውን ሥራ ላይ ለማዋል ከአንዱ አገር ወደሌላው በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ የተጨማሪ እሴት ታክስን ባህሪያት ጠንቅቀው ስለሚያውቁ በቀላሉ ለመግባባት ምቹ ሁኔታን የፈጠረ ሲሆን፤ የሰዎች እና የዕቃዎች እንቅስቃሴ የተሳለጠ እንዲሆን አድርጓል፡፡

በአገራችንም የተጨማሪ እሴት ታክስ ከ1994 ዓ.ም ጀምሮ ሥራ ላይ የዋለ ሲሆን፤ በአፈፃፀም በርካታ ችግሮች ያሉ ቢሆንም ከአገር ውስጥ ቀጥተኛ ያልሆኑ ታክሶች የሚሰበሰበው ገቢ መቶኛ በየጊዜው እየጨመረ እንዲሄድ የተጨማሪ እሴት ታክስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡

በ1994 ዓ.ም የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ከወጣ ወዲህ ለሁለት ጊዜያት ያህል መጠነኛ ማሻሻያዎች የተደረጉ ቢሆንም በኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ላይ በመደረግ ላይ ያሉ ለውጦችን ተከትሎ የተሟላ ማሻሻያ ሳይደረግበት ከ22 ዓመት በላይ ያስቆጠረ በመሆኑ ጊዜውን የዋጀ ማሻሻያ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

  1. የማሻሻያው ዓላማ

የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ማሻሻያ አዋጅ የሚከተሉትን ዓላማዎች ለማስፈፀም የተዘጋጀ ነው፡፡

  1. የተጨማሪ እሴት ታክስ ሥራ ላይ ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ በአገሪቱ የኤኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ የተደረጉ ለውጦችን ያገናዘበ የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ እንዲኖር ማድረግ፤

  2. የታክስ መርሆዎችን በተከተለ መንገድ የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅን በቀላሉ መረዳት በሚያስችል አኳኋን መቅረፅ፤

  3. በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ የሚፈፀሙ ግብይቶች ተገቢው ታክስ እንዲሰበሰብባቸው ማድረግ የሚያስችል የተጠናከረ የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት፤


  1. ዝቅተኛ ገቢ ያለው የህብረተሰብ ክፍል የታክሱ ጫና እንዳያርፍበት የተፈቀዱ ከታክስ ነፃ የመሆን መብቶች ተጠቃሚ እንዲሆን የታቀደውን የህብረተሰብ ክፍል ብቻ እንዲመለከቱ ማድረግ፤

  2. ከታክስ ነፃ የመሆን መብቶች በግብዓት ታክስ እና በውጤት ታክስ መካከል ያለውን ሰንሰለት የጠበቁ እንዲሆኑ ማድረግ ዋና ዋና ዓላማዎቹ ናቸው፡፡

  1. የማሻሻያው ዋና ዋና ነጥቦች

    1. አዋጁን በቀላሉ መረዳት በሚያስችል አኳኋን መቅረፅ በማስፈለጉ፡-

በየቀድሞው የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር 285/1994 ካሉበት ችግሮች አንዱ በአቀራረፁ ውስብስብነት ምክንያት የታክሱ ባለሥልጣን ባለሙያዎች እና ታክስ ከፋዩ ህብረተሰብ በቀላሉ ሊረዱት ያለመቻል ነው፡፡

ይህ ችግር በታክስ ከፋዮች እና በታክስ ባለሥልጣን መካከል በግብር አከፋፈል ረገድ ለሚፈጠረው ያለመግባባት ዋንኛው መንስኤ ሆኖ በመገኘቱ የታክስ ሥርዓቱ የተሳለጠ እንዲሆን አቀራረፁን ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

በዚህም መሠረት፡-

  1. አዋጁን የጉዳዮችን ምክንያታዊ ፍሰት (logical flow) በተከተለ አኳኋን የማዋቀር፤ አዋጁ የሚከተላቸው አጠቃላይ መርሆዎች ተለይተው እንዲታዩ የማድረግ፤ ከአጠቃላይ መርሆዎች የተለዩ ሁኔታዎችን (ለምሳሌ፤ የግብዓት ታክስን የሚመለከት ድንጋጌዎች) ራሳቸውን አስችሎ የመደንገግ፤

  2. ለተጨማሪ እሴት ታክስ በተመዘገቡ ሰዎች ላይ ሁሉ ተፈፃሚነት የሚኖራቸውን የአዋጁን መሠረታዊ ድንጋጌዎች በቀላሉ መረዳት በሚያስችል መንገድ በአዲሱ አዋጅ ቁጥር 1341/2016 የመቅረፅ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡

  3. ከዚህም በተጨማሪ በታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 ላይ ለቃላት እና ሐረጎች የተሰጠው ትርጉም ለተጨማሪ እሴት ታክስ ጭምር የሚያገለግል በመሆነ፤ በታክስ አስተዳደር አዋጅ ትርጉም የተሰጣቸው ቃላት እና ሐረጎች ከትርጉም ክፍል እንዲወጡ ተደርጓል፡፡

  1. አዲሱ የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር 1341/2016 መሠረታዊ ድንጋጌዎችን እና የአስተዳደር ድንጋጌዎችን መለየት ችሏል፤

    1. ከጉምሩክ በስተቀር የሁሉንም የታክስ ዓይነቶች አስተዳደር የሚመራ የታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 ሥራ ላይ የዋለ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም አብዛኛዎቹ የተጨማሪ እሴት ታክስን አስተዳደር የሚመሩ ድንጋጌዎች በታክስ አስተዳደር አዋጅ ውስጥ የተካተቱ በመሆኑ፤ ከተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ እንዲወጡ ተደርጓል፡፡

    2. በተጨማሪ እሴት ታክስ ደንብ ቁጥር 79/95 ውስጥ ተካተው የነበሩ መሠረታዊ ድንጋጌዎች ወደ አዋጁ እንዲመጡ ተደርጓል፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚሰጠው ሥልጣን መሠረት የሚያወጣው ደንብ ለአዋጁ ትክክለኛ አፈፃፀም የሚረዱ ድንጋጌዎችን ከሚይዝ በስተቀር አዳዲስ ግዴታዎችን የሚጥል ሊሆን አይገባም፡፡ በዚህም መሠረት በደንቡ ውስጥ ተካተው የነበሩ መሰረታዊ ድንጋጌዎች ፤ በተለይም፤


  1. ታክሱን የማስታወቅ እና የመክፈል ግዴታ፤

  2. የሂሳብ መዝገብ አያያዝ፤

  3. የታክስ ደረሰኝ፤

  4. ዴቢት/ክሬዲት ሰነድ፤ ወደ አዋጁ እንዲመጡ ተደርጓል፡፡

  1. የአዋጁ ተፈፃሚነት ወሰን

የተጨማሪ እሴት ታክስ በባህሪው የፍጆታ ታክስ ነው፡፡ በመሆኑም የታክሱ የመጨረሻ ከፋዮች ሸማቾች ናቸው፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ በንግድ ሥራ የተሰማሩ ነጋዴዎች የሚጠበቅባቸው ታክሱን ከሸማቹ በመሰብሰብ ለመንግሥት ገቢ እንዲያደርጉ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ንግድ ግንኙነት ወቅት ታክሱ ያለው አፈፃፀም አገር ውስጥ ከሚቀርቡ አቅርቦቶች የተለየ ነው፡፡ በዚህ መሠረት የተጨማሪ እሴት ታክስን አጣጣል በሚመለከት ኢትዮጵያ የምትከተለው የመዳረሻ መርህን (Destination Principle) በመሆኑ፤ ታክሱ የሚጣለው ዕቃዎቹ ጥቅም ላይ በሚውሉበት አገር ነው፡፡ በመሆኑም በአዲሱ አዋጅ መሠረት ታክሱ ተፈፃሚ የሚሆነው በኢትዮጵያ ውስጥ ጥቅም ላይ በሚውሉ ዕቃዎች እና አገልግሎቶች ላይ ብቻ እንጂ ወደ ውጭ አገር በሚላኩ ዕቃዎች እና አገልግሎቶች ላይ አይደለም፡፡

በዚህ መሠረት አዋጁ ተፈፃሚ የሚሆንባቸውን በዝርዝር ለይቶ ማስቀመጡ አስፈላጊ ነው፡፡ 

በመሆኑም አዋጁ ተፈፃሚ የሚሆነው፤

  1. በኢትዮጵያ የግዛት ክልል ውስጥ በሚከናወኑ ታክስ የሚከፈልባቸው የዕቃ እና/ወይም የአገልግሎት አቅርቦቶች፣

  2. ታክስ የሚከፈልባቸው ወደ አገር የሚገቡ ማናቸውም ዕቃዎች፤ እና

  3. በቀጥታ በገዢው ታክስ በሚከፈልበት ኢትዮጵያ ውስጥ ቋሚ የሥራ ቦታ በሌለው ሰው ከውጭ አገር ሆኖ ኢትዮጵያ ውስጥ ላለ ሰው በሚከናወን ታክስ የሚከፈልበት አቅርቦት ላይ ነው፡፡

ሦስተኛውን በተመለከተ አንዳንድ የአገልግሎት አቅራቢዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ምንም ዓይነት የሥራ አድራሻም ሆነ የንግድ ፈቃድ ሳይኖራቸው በኢትዮጵያ ለሚገኙ የተለያዩ የመንግስት እና የግል መስሪያ ቤቶች አገልግሎቶችን ያቀርባሉ፡፡ ለምሳሌ ያክል የተለያዩ ሶፍትዌሮችን ከኦራክል፣ ማይክሮሶፍት እና ሌሎች የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የመንግስት እና የግል መስሪያ ቤቶች ግዥ ይፈጽማሉ፡፡ የዚህ ዓይነቱ አገልግሎት በኢትዮጵያ ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውል በመሆኑ ታክሱ ይመለከታቸዋል፡፡ 

በመሆኑም በአዲሱ አዋጅ ለታክሱ አሰባሰብ ሲባል፦

  1. በአንድ ዓመት ውስጥ ኢትዮጵያ ነዋሪ ለሆኑ ድርጅቶች የውጭ ኩባንያ የሚፈጽመው አቅርቦት ዋጋ በህግ ለምዝገባ ከተቀመጠው የገንዘብ መጠን በላይ ከሆነ አቅርቦቱ የሚፈጸምለት ኢትዮጵያ ነዋሪ የሆነው ድርጅት ለተጨማሪ እሴት ታክስ ተመዝግቦ ከተከፋይ ሂሳብ ላይ ታክሱን ቀንሱ እንዲያስቀር፣ እና 

  2. አቅርቦቱ የሚፈጸመው የመመዝገብ ግዴታ ለሌለባቸው ሰዎች ከሆነ አቅራቢው የውጭ ኩባንያ ለታክሱ እንዲመዘገብ፤ ታክሱን ሰብስቦ ገቢ እንዲያደርግ እና የታክስ ተወካዩን እንዲያስመዘግብ ይገደዳል፡፡



  1. ታክስ የሚከፈልበት ግብይት

የተጨማሪ እሴት ታክስ በግብይት ላይ የሚከፈል ታክስ እንደመሆኑ ታክሱ የተጣለበትን ግብይት በግልጽ መደንገግ አስፈላጊ ይሆናል። 

በዚህም መሠረት ታክሱ የሚከፈለው፧

  1. የንግድ ባህርይ ያለው ከሆነ ለአንድ ጊዜ የሚከናወንን የሚጨምር መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ተፈፃሚ የሚሆነው በተከታታይነት ወይም በመደበኛነት በሚከናወን ግብይት ላይ መሆኑ፤ 

  2. ነዋሪ ባልሆነ የሚሰጥን አገልግሎት እንደሚጨምር፤ 

  3. የቅጥር አገልግሎትን እንደማይጨምር፤ ግልፅ ተደርጓል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በተጨማሪ እሴት ታክስ ደንብ ቁጥር 79/1995 አንቀጽ 4(2) በግለሰብ የሚሰጥ የመዝናኛ አገልግሎትን እንደማይጨምር የተመለከተው መሠረታዊ በመሆኑ ወደ አዋጁ እንዲመጣ፤ ታክስ የሚከፈልበትን ግብይት ለመጀመር ወይም ለማቋረጥ የሚከናወን ተግባር ታክስ የሚከፈልበት ግብይት እንደሚሆን በደንቡ አንቀጽ 4(1) የተመለከተው ወደ አዋጁ እንዲመጣ፤ እንዲሁም ከታክሱ ነፃ የሆነ ግብይት ታክስ የሚከፈልበት ግብይት እንደማይባል በደንቡ አንቀጽ 4(2)(ለ) የተመለከተው ወደ አዋጁ እንዲመጣ ተደርጓል፡፡

  1. ተጨማሪ እሴት ታክስ የሚጣልበት ዋጋ

የተጨማሪ እሴት ታክስን በመሰብሰብ ረገድ ዋጋ መሠረታዊ ሲሆን፤ በአፈፃፀም ላይ ግን ከፍተኛ ችግር የሚታይበት ጉዳይ ነው፡፡

በአዲሱ አዋጅ “የአቅርቦት ዋጋ” የታክሱን መጠን ለመወስን እንዲሁም ታክስ ከፋዩ የመመዝገብ ግዴታ ያለበት መሆን ያለመሆኑን ለመወሰን የሚያገለግል በመሆኑ ግልፅ የሆነ ትርጓሜ እዲሰጠው ተደርጓል፡፡

በዚህም መሠረት ዋጋ (consideration or price) የሚለው ቃል በአዋጁ የትርጉም ክፍል እንደሚከተለው ተተርጉሟል፤

  1. ማናቸውም ሰው በቀጥታ ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ለአቅርቦቱ የከፈለው ወይም የሚከፍለው የገንዘብ መጠን፤ 

  2. ዕቃ አቅርቦትን በሚመለከት የዕቃው አቅርቦት ለተፈጸመበት የዕቃ መያዣ የተከፈለውን ወይም የሚከፈለውን እና የዕቃው መያዣ ሲመለስ ተመላሽ የሚደረገውን ተቀማጭ ገንዘብ፤

  3. ለአቅርቦቱ የተከፈለው ወይም የሚከፈለው የአገልግሎት ክፍያ፣ እና

  4. በአቅርቦቱ ምክንያት የተከፈለው ወይም የሚከፈለው ማናቸውም ቀረጥ፤ የኤክሳይዝ ታክስ፣ ሱር ታክስ፣ የአገልግሎት ክፍያ እና ሌሎች ክፍያዎችን አካቷል፡፡

  1. በገዢው የሚሰበሰብ ታክስ

    1. የተጨማሪ እሴት ታክስ የፍጆታ ታክስ እንደመሆኑ በአገር ውስጥ ወይም ከውጭ አገር በቀረበ ዕቃ ወይም በተሰጠ አገልግሎት ላይ ተፈፃሚ መሆን አለበት፡፡ ከውጭ አገር የሚቀርብ ዕቃ በመግቢያ በሮች በጉምሩክ አማካኝነት ታክሱ የሚሰበሰብበት ሊሆን፤ ከውጭ አገር በሚሰጥ፤

    2. አገልግሎት ላይ አገልግሎት ተቀባዩ ራሱ ታክሱን ሰብስቦ ለገቢ ሰብሳቢው ባለሥልጣን መክፈል ይኖርበታል፡፡

    3. ከውጭ አገር የተሰጠ አገልግሎት የሚባለው፤

    4. የአገልግሎቱ አቅራቢ ለተጨማሪ እሴት ታክስ ያልተመዘገበ ከሆነ፤

    5. አገልግሎቱ የተሰጠው ከኢትዮጵያ ውጪ ሲሆን፤

    6. አገልግሎቱ ታክስ ለሚከፈልበት የስራ እንቅስቃሴ የዋለ እና ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ ያልተደረገ ሲሆን ነው፡፡

    7. በዚህም መሠረት የአገልግሎቱ ተቀባይ የታክስ ደረስኝ (Recipient created tax invoice) በመቁረጥ ታክሱን ለግብር ሰብሳቢው ባለሥልጣን ገቢ ማድረግ አለበት፡፡ በውጭ አገር የሚገኝ ዋና መስሪያ ቤቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ላለ ድርጅቱ የሚሰጠው አገልግሎትም በዚሁ መሠረት ይሸፈናል፤






በአዲሱ የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር 1341/2016 የተካተቱ፣ በቀድሞው የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር 285/1994 ላይ የተደረጉ ለውጦች  (The new Ethiopian VAT proclamation no. 1341/2024)





  1. ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ የመሆን መብት - አጠቃላይ ማስተካከያዎች

የቀድሞው የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር 285/1994 ከሚታይበት ጉድለት አንዱ እና ዋንኛው በርካታ ዕቃዎች እና አገልግሎቶች ከታክሱ ነፃ እንዲሆኑ መደረጋቸው ነው፡፡ በአዋጁ እና በአዋጁ ለገንዘብ ሚኒስቴር በተሰጠው ሥልጣን ከታክሱ ነፃ የተደረጉ ዕቃዎች እና አገልግሎቶች ዋንኛ ዓላማ ታክሱ ዝቅተኛ ገቢ ባለው የህብረተሰብ ክፍል ላይ ሊያሳድር የሚችለውን ጫና መከላከል እና የወጪ ንግድን ማበረታታት ቢሆንም ልዩነት ሳይደረግ ሁሉም ሰው ከታክሱ ነፃ በመሆኑ ዓላማውን ስቶ ነበር፡፡

በእነዚህ ምክንያቶች ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ በማድረግ ረገድ የተሰጠውን ልዩ መብት እንደገና በመፈተሽ የሚከተሉት አጠቃላይ ማስተካከያዎች ተደርገዋል፡፡

  1. ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ ተደርገው ከነበሩት መካከል በቂ ምክንያት ያልተገኘላቸው ታክሱ እንዲከፈልባቸው ማድረግ፤

  2. በማህበራዊ ምክንያት ከታክሱ ነፃ የተደረገው ዝቅተኛ ገቢ ያለውን የህብረተሰብ ክፍል ብቻ በሚጠቅም ዓይነት እንዲስተካከል ማድረግ፤

  3. ለገንዘብ ሚኒስቴር ተሰጥቶ የነበረው ከታክስ ነፃ የማድረግ ሥልጣን በምግብ አቅርቦቶች ብቻ እንዲወሰን ማድረግ፤

  4. ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ የመሆን መብት በቀጥታ ጥቅም ላይ ለሚውሉ የመጨረሻ ምርቶች እንጂ ለግብአቶች (intermediate) ተፈፃሚ እንዳይሆን ማድረግ፤

  1. ከታክሱ ነፃ የተደረጉ የፋይናንስ አገልግሎቶች

የፋይናንስ ተቋማት ቁጠባን በማበረታታትና ኢንቬስትመንትን በመደገፍ ረገድ ያላቸውን አስተዋፅኦ እንዲሁም በአንዳንድ የፋይናንስ ግብይቶች የተጨማሪውን እሴት መለየት አስቸጋሪ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት በቀድሞው የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር 285/1994 የፋይናንስ ተቋማት ከሚሰጧቸው አገልግሎቶች ውስጥ አብዛኛው ከታክሱ ነፃ ተደርገው ቆይተዋል፡፡


ይሁን እንጂ በፋይናንስ ተቋማት ከሚሰጡት አገልግሎቶች ውስጥ አብዛኛዎቹ የታክስ ነፃ መብቱ ከተሰጠበት ዓላማ ጋር የማይገናኙ በመሆኑ፤ ከታክስ ነፃ የመሆን መብት ሊቋቋምላቸው የሚገባውን ለይቶ በመዘርዘር (positive list) ከዚያ ውጭ ያሉት ታክሱ እንዲከፈልባቸው ማድረግ የተሻለ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

በዚህም መሠረት፤

ለፋይናንስ አገልግሎት የተሰጠው ከታክስ ነፃ የመሆን መብት ተቋሙን ሳይሆን የአገልግሎቱን ባህሪ እንዲመለከት በማድረግ የተሰጠው ከታክሱ ነፃ የመሆን መብት ተፈፃሚ የሚሆነው ፤

  1. ብድር ከመስጠት፤ ከመሰብሰብ፣

  2. ከተቀማጭ ገንዘብ (deposit)

  3. አክሲዩን፤ ቦንድ፤ ሌሎች የዋስትና ሰነዶች ከመገበያየት፤

  4. የኢንቬስትመንት ፈንድ ከማስተዳደር፤

  5. የጡረታ ፈንድ ከማቋቋም፤ ጋር የተያያዘው ብቻ እንዲሆን ተደርጓል፤

  6. በሸሪያ ሕግ መሠረት ከሚሰጡ የፋይናንስ አገልግሎቶች ውስጥ ደግሞ በቀጣይ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣው ደንብ ተለይተው የሚዘረዘሩት ከታክሱ ነፃ እንዲሆኑ ተደርጓል፤

የፋይናንስ ተቋማት በተወሰነ ክፍያ (ኮሚሽን፤ የአገልግሎት ክፍያ (fee) የሚሰጡዋቸው አገልግሎቶች ከታክሱ ነፃ ከተደረጉት መካከል እንዳይካተቱ ተደርጓል፡፡

  1. የመድን አገልግሎት

የመድን አገልግሎት ልዩነት ሳይደረግበት ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ መደረጉ በቂ ምክንያት የሌለው እና ከሌሎች አገሮች ልምድም ጋር የማይጣጣም ሆኖ ተገኝቷል፡፡

በዚህም ምክንያት በመድን ሥራዎች አዋጅ በተተረጎመው መሠረት ከረዥም ጊዜ መድን ( ከህይወት እና ጤና መድን) በስተቀር ሌላ ማናቸውም አጠቃላይ የመድን ፖሊሲ ለመግዛት የሚከፈል ፕሪሚየም እና ጉዳት በሚደርስበት ጊዜ የሚከፈል ካሳ በአዋጁ መሠረት ግብይት ስለሆኑ፤ ታክሱ እንዲከፈልባቸው ተደርጓል፡፡ የህይወት እና የጤና መድን ግን ከህብረተሰቡ ማህበራዊ ዋስትና ጋር የተያያዘ በመሆኑ ከታክሱ ነፃ እንዲሆን ተደርጓል፡፡

አጠቃላይ መድን ታክስ የሚከፈልበት በመሆኑ የመድን ድርጅቶች ሥራቸውን ለማከናወን የሚያስፈልጓቸውን ዕቃዎች እና አገልግሎቶች ግዢ በሚፈፅሙበት ጊዜ የከፈሉትን የተጨማሪ እሴት ታክስ ማቀናነስ የሚችሉበትን እድል ሰለሚፈጥር ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡

  1.  በመኖሪያነት ያገለገለ ቤት

የከተማ ነዋሪ የሆነው ዝቅተኛ ገቢ ያለው የህብረተሰብ ክፍል ካሉበት ችግሮች አንዱ እና ዋንኛው የመኖሪያ ቤት ችግር እንደሆነ ይታወቃል፡፡

በመሆኑም ህብረተሰቡ ያለበትን የመኖሪያ ቤት ወጪ ጫና በመጠኑም ቢሆን ለማቃለል እንዲቻል ቢያንስ ለሁለት ዓመታት በመኖሪያነት ያገለገለ ቤት ሽያጭ እንዲሁም የመኖሪያ ቤት ኪራይ በቀድሞው አዋጅ ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ ሆኖ ቆይቷል፡፡ የዚህ ዓይነቱ እገዛ አስፈላጊ እና በሌሎች አገሮችም የሚደረግ በመሆኑ በነበረበት እንዲቀጥል ተደርጓል፡፡

  1. የትራንስፖርት አገልግሎት

የትራንስፖርት አገልግሎት ከታክሱ ነፃ እንዲሆን የተደረገው አነስተኛ ገቢ ያለው የህብረተሰብ ክፍል ለትራንስፖርት የሚያወጣው ወጪ እንዳይንር እንዲሁም በጭነት ተሽከርካሪዎች ላይ የሚከፈለው ታክስ የዕቃዎችን ዋጋ መናር እንዳያስከትል ለማድረግ ነው፡፡

ሆኖም ከህዝብ ትራንስፖርት ውጪ ለሌሎች የትራንስፖርት አገልግሎቶች የዚህ ዓይነቱን ድጋፍ ማድረግ ተገቢ ባለመሆኑ ለትራንስፖርት አገልግሎት የተሰጠው ከታክሱ ነፃ የመሆን መብት ባለሦስት እግርን ሳይጨምር ከስምንት መቀመጫ በታች ያላቸውን ሌሎች ተሽከርካሪዎች እንዳይመለከት ተደርጓል፡፡ ነገር ግን የእነዚህ ዓይነት የትራንስፖርት ሰጪ አካላት ዓመታዊ ሽያጭ ከብር 2,000,000.00 (ሁለት ሚሊዮን) በላይ መሆን አለበት፡፡

  1.  የኤሌክትሪክ እና የውሃ አገልግሎት

የኤሌክትሪክ እና የውሃ አቅርቦት ከታክሱ ነፃ ተደርጎ የነበረው አነስተኛ ገቢ ያለው የህብረተሰብ ክፍል ያለበትን የወጪ ጫና ለማርገብ ሲባል ነው፡፡

ይሁን እንጂ ኤሌክትሪክ እና ውሃ በብዛት የሚጠቀመው የመክፈል ዓቅም ያለው የህብረተሰብ ክፍል በመሆኑ የተሰጠው መብት ይበልጥ ተጠቃሚ የሆነው ይህ የህብረተስብ ክፍል ነው፡፡ ይህ የህብረተሰብ ክፍል ደግሞ ታክሱ የሚያስከትልበት የወጪ ጫና የሌለ በመሆኑ ድጋፉ ትርጉም ያለው አይደለም፡፡

በመሆኑም ድጋፉ ታሳቢ ያደረገውን የህብረተሰብ ክፍል ብቻ በሚጠቅም መልኩ ማስተካከያ ማድረግ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ በዚህም መሠረት ከታክሱ ነፃ የመሆኑ መብት ተጠቃሚ የሚሆኑት የገንዘብ ሚኒስቴር በሚያወጣው መመሪያ ከሚወሰን በታች የኤሌክትሪክ እና የውሃ ፍጆታ ያላቸው እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡

  1.  የኤሌክትሮኒክስ ግብይት

የህብረተሰብ ግንኙነት የተሳለጠ እንዲሆን ቴክሎኖሎጂ ከፍተኛ እገዛ በማድረግ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ በዚህ ረገድ ሊጠቀሱ ከሚችሉት አንዱ የኤሌክትሮኒክስ ንግድ ነው፡፡

የኤሌክትሮኒክስ ንግድ የአገራችንን የንግድ ዘይቤ በማዘመን ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ሲሆን፤ ብቃት ያለው የመከታተል ሥርዓት ከተበጀለት ከታክሱ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ እና የታክስ ማጭበርበርን ለመከላከልም እገዛ ይኖረዋል፡፡

በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ ግብይት ከሚካሄድባቸው መካከል በድረ-ገጽ፤ በኢንተርኔት፤ በፖርታል፤ በጌትዌይ፤ በመደብር (ስቶር)፤ በገበያ ቦታ ወይም በሌላ ማናቸውም አቅራቢ ከሩቅ ሆኖ በሩቅ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ወይም በኤሌክትሮኒክ ዘዴ የሚታዘዙ ዕቃዎችን በሌላ ሰው አማካኝነት ለሦስተኛ ሰው የሚቀርብበት በኤሌክትሮኒክ ዘዴ የሚሰራ ሌላ ተመሳሳይ የኤሊክትሮኒክስ ገበያ ይገኝበታል፡፡

በመሆኑም በእነዚህ ገበያዎች የሚከናወን ግብይት የተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲሰበሰብበት ማድረግ የሚያስችሉ ድንጋጌዎች በአዋጁ ተካተዋል፡፡ በዚህም መሠረት የሌሎችን ምርቶች ለገበያ የሚያቀርቡ እንደ አማዞን፤ ጉግል ፕሌይ፤ አፕል ስቶር የመሳሰሉት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚያከናውኑትን ግብይት በሚመለከት ለተጨማሪ እሴት ታክስ መመዝገብ እንዳለባቸው፤ እነዚህ የውጭ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ውስጥ የባንክ ሂሳብ መክፈት ያለባቸው መሆኑን፤ ባንኩ ለኩባንያዎቹ ከሚከፍለው ሂሳብ ላይ ታክሱን ቀንሶ ማስቀረት እንዳለበት ተደንግጓል፡፡

ኩባንያዎቹ በማናቸውም ምክንያት ያልተመዘገቡ ከሆነ ከእነዚህ የውጭ ኩባንያዎች በየዓመቱ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ ከሩቅ የሚሰጥ አገልግሎት የሚያገኝ ለታክሱ ያልተመዘገበ በኢትዮጵያ ነዋሪ የሆነ ሰው መመዝገብ እንዳለበት እና ታክሱን እራሱ ከሚከፍለው ገንዘብ ላይ አስልቶ መክፈል እንዳለበት የሚደነግጉ አንቀፆች ተካተዋል፡፡

  1.  ታክሱን የመሰብሰብ ሥልጣን

በአዲሱ አዋጅ የተጣለው የተጨማሪ እሴት ታክስ የሚወሰነው እና የሚሰበሰበው እንደ አግባብነቱ በገቢዎች ሚኒስቴር ወይም በጉምሩክ ኮሚሽን ይሆናል፡፡ ሆኖም የገቢዎች ሚኒስቴር ስለእርሱ ሆነው የተጨማሪ እሴት ታክስን እንዲወስኑ እና እንዲሰበስቡ ለክልል እና ለከተማ አስተዳደር የገቢዎች ቢሮዎች ውክልና ሊሰጥ ይችላል በሚል በአዲሱ አዋጅ ተደንግጓል፡፡

  1.  የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት

የቴሌ ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ለማግኘት የሚያስችሉ ካርዶችን እና ሌሎችንም አቅርቦቶች በማከፋፈል ረገድ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚሳተፉ በመሆኑ እነዚህን ታክስ ከፍዮች መዝግቦ ታክሱን እንዲሰበስቡ ማድረግ ውስብስብ አስተዳደራዊ ችግርን ያስከትላል፡፡

በመሆኑም አስተዳደሩን ምቹ እና ቀላል ለማድረግ የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት የሚሰጥ ኩባንያ ለወኪሎቹ የሚሰጠው ቅናሽ ከግምት ውስጥ ሳይገባ ታክሱን በሙሉው ዋጋ ላይ እንዲሰበስብ እና ወኪሎቹ ታክሱን ከመሰብሰብ ግዴታ ነፃ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡

ሌላው ከቴሌኮሚኒኬሽን የተጨማሪ እሴት ታክስ በመሰብሰብ ረገድ አከራካሪ የነበረው በውጭ አገር የሚሰራ የኢትዮጵያ ሲም ካርድ (የሮሚንግ ስልክ) በመጠቀም የሚገኝ አገልግሎት ታክሱ የሚከፈልበት በኢትዮጵያ ነው ወይስ ስልኩ ጥቅም ላይ በዋለበት አገር? የሚለው ጥያቄ ነበር፡፡ የዓለም አቀፍ ተሞክሮን ከግምት ውስጥ በማስገባት ታክሱ የሚከፈለው በኢትዮጵያ መሆኑ ግልጽ እንዲሆን ተደርጓል፡፡

  1. የቱሪዝም አገልግሎት

በቱሪስት አስተጋጅነት ሥራ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች (tour operators) ቱሪስቶችን በማስተናገድ ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ በመሆኑ እንደማናቸውም ኤክስፖርት ዜሮ የማስከፈያ ልክ ተፈፃሚ እንዲደረግላቸው ከረዥም ጊዜ ጀምሮ ጥያቄ ሲያቀርቡ የነበረ በመሆኑ ለዚህ ጥያቄ ምላሽ መስጠት የሚያስችል ጥናት ተደርጓል፡፡

በጥናቱም የተጨማሪ እሴት ታክስ ፍጆታው የተከናወነበትን ቦታ መርህ (destination principle) የሚከተል ስለሆነ መለኪያው አገልግሎቱ የተሰጠው ለማነው? ወይም ውጭ ምንዛሪ ተገኝቶበታል ወይስ አልተገኘበትም? ሳይሆን የዕቃው ወይም የአገልግሎቱ ፍጆታ የተከናወነው የት ነው? የሚለው ነው፡፡ በመሆኑም ለቱሪስቶች አገልግሎት የሚሰጠው በኢትዮጵያ ውስጥ ስለሆነ አቅርቦቱ እንደ ኤክስፖርት እንዲቆጠር ማድረግ የሚያስችል ምክንያት የለም፡፡

የዘርፉ ሁለተኛው ጥያቄ ቱሪስቶች በቡድን ወደ አገር መጥተው የጥቅል የቱሪዝም አገልግሎት በሚያገኙበት ጊዜ ከተከፈለው ጥቅል ገንዘብ ውስጥ አብዛኛው ለመኝታ፤ ለምግብ፤ ለትራንስፖርት ወ.ዘ.ተ. የሚውል በመሆኑ አስጎብኚዎቹ የምናገኘው ቀሪውን ሂሳብ ስለሆነ ታክሱ ሊሰላ የሚገባው በቀሪው ሂሳብ ወይም በኮሚሽኑ ላይ መሆን አለበት የሚል ነው፡፡

ከዚህ በላይ እንደተገለፀው የተጨማሪ እሴት ታክስ በዓለማችን ተመራጭ የታክስ ዓይነት የሆነው ግብይቱ መቆጣጠር የሚያስችል የራሱ የሆነ ሥርዓት (inbuilt mechanism) ያለው በመሆኑ ምክንያት ነው፡፡ በመሆኑም ታክሱ በጥቅል ክፍያው ላይ ተሰብስቦ ለመኝታ፤ ለምግብ ወ.ዘ.ተ ገንዘብ ወጪ ሲደረግ የተከፈለው ታክስ ከሚቀናነስ በስተቀር ከተከፈለው ሂሳብ ላይ የማቀናነስ አስራር ከተጨማሪ እሴት ታክስ ባህሪ ጋር የማይሄድ ሰለሆነ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም፡፡

ይሁን እንጂ በአዲሱ አዋጁ አንቀጽ 74 ንኡስ አንቀጽ 7 “በዚህ አዋጅ የተደነገገው ቢኖርም በቱሪስት አስጎብኚነት የንግድ ሥራ ላይ የተሰማራ የተመዘገበ ሰው ይህ አዋጅ ከፀናበት ቀን አንስቶ ለሦስት ዓመታት ያህል የተጨማሪ እሴት ታክስ የሚከፍለው በአገር ውስጥ ጥቅል የቱሪዝም አገልግሎት ለመስጠት ከተቀበለው ክፍያ ላይ ለመኝታ፤ ለምግብ እና ለትራንስፖርት የሚያወጣው ወጪ ተቀንሶ በሚቀረው ሂሳብ ወይም በሚከፈለው ኮሚሽን ላይ ይሆናል፡፡' በሚል የመሸጋጋሪያ ጊዜ ድንጋጌ ተቀምጧል፡፡

ከዚያ በኋላ ግን የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ድንጋጌዎችን እና ዓለም አቀፍ ተሞክሮን በተከተለ መንገድ ታክሱ በጥቅል ገቢው ላይ ተሰልቶ የማቀናነስ ሥርዓት ተፈፃሚ እንዲሆን በሚያስችል መንገድ በአዲሱ አዋጅ ተቀርጿል፡፡

  1.  የመክፈያ ጊዜ

የግብር አከፋፈል ሥርዓታችን በቴክኖሎጂ ያልተደገፈ ሰለነበር ግብር ከፋዩ በየወሩ የሰበሰበውን ታክስ ለማስታወቅ እና ለመክፈል በገቢ ሰብሳቢው ባለሥልጣን ዘንድ መመላለስ ነበረበት፡፡ ይህንን ምልልስ በመቀነስ ለታክስ ከፋዮች እፎይታን ለማስገኘት ሲባል፤ በአዋጁ ማሻሻያ ታክስ የሚከፈልበት ዓመታዊ ግብይታቸው ከ70 ሚሊዮን ብር በታች የሆነ ግብር ከፋዩች የሰበሰቡትን ታክስ የሚያስታውቁት እና የሚከፍሉት በየሦስት ወሩ እንዲሆን ተደርጎ ነበር ፡፡

ይሁን እንጂ ይህ ታክስ ማስታወቅ እና መክፈል በቴክኖሎጂ የተደገፈ እንዲሆን ማድረግ የተቻለ በመሆኑ የመክፈያው የጊዜ ገደብ ሦስት ወር እንዲሆን የተደረገበት ምክንያት በአሁኑ ወቅት የማይሰራ በመሆኑ ከዚህ ቀደም ሲሠራበት እንደነበረው ሁሉም ታክስ ከፋዮች የሰበሰቡትን ታክስ በየ30 ቀኑ እንዲያስታውቁ እና እንዲከፍሉ ተደርጓል፡፡

  1.  ለተጨማሪ እሴት ታክስ ሰለመመዝገብ

በቀደመው አዋጅ ለተጨማሪ እሴት ታክስ የመመዝገብ ግዴታ ያለባቸው ዓመታዊ ታክስ የሚከፈልበት ግብይታቸው ከብር 1,000,000.00 (አንድ ሚሊዮን) በላይ የሆኑ ታክስ ከፋዮች ነበሩ፡፡


ይሁን እንጂ የገንዘብ የመግዛት ዓቅም እየተዳከመ መሄዱን ከግምት ውስጥ በማስገባት ይህ የገንዘብ መጠን ወደ ብር 2,000,000.00 (ሁለት ሚሊዮን) ከፍ እንዲል ተደርጓል፡፡ በመሆኑም ከዚህ የገንዘብ መጠን በታች ግብይት ያላቸው ታክስ ከፋዮች የሚሰበስቡት የተርን ኦቨር ታክስ ይሆናል፡፡

በቀድሞው አዋጅ ታክስ ከፋዮች የተጨማሪ እሴት ታክስ የማቀናነስ ሥርዓት ተጠቃሚ ለመሆን ሲሉ ግብይታቸውን ለተጨማሪ እሴት ታክስ ከተመዘገበ ሰው ጋር ማድረግን ይመርጣሉ፡፡ በመሆኑም ያልተመዘገቡ ሰዎች ከገበያ ውጪ እንዳይሆኑ በማሰብ ከግብይታቸው 75% የሚሆነው ለተጨማሪ እሴት ታክስ ከተመዘገቡ ታክስ ከፋዩች ጋር የሆነ አነስተኛ ታክስ ከፋዮች በፈቃደኝነት እንዲመዘገቡ ሲደረግ ቆይቷል፡፡

ይሁን እንጂ ታክስ ከፋዮች 75% የሚሆነው ግብይታቸው ለተጨማሪ እሴት ታክስ ከተመዘገቡ ጋር መሆኑን ለማስረዳት ችግር ሰለሚያጋጥማቸው እንዲሁም ለወደፊት ሁሉም ታክስ ከፋይ ለተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲመዘገብ ማድረግ ስለማይቀር ዓመታዊ ታክስ የሚከፈልበት ግብይታቸው ከብር 1,000,000.00 (አንድ ሚሊዮን) በላይ የሆነ ሁሉ በፈቃደኝነት እንዲመዘገቡ ተደርጓል፡፡

  1. ማጠቃለያ

አዲሱ የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ከ22 ዓመታት በላይ ሥራ ላይ የቆየው አዋጅ የነበሩበትን ጉድለቶች የሚያርም እና ታክስ ከፋዩ ህብረተሰብ በቀላሉ ሊረዳው እና ሊፈፅመው የሚያስችል ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ግልጽነት በጎደላቸው አንቀፆች ምክንያት በታክስ ከፋዩ እና በታክስ ሰብሳቢው መስሪያ ቤት መካከል ሲፈጠር የነበረውን ያለመግባባት በማስወገድ ምቹ የሆነ የታክስ አስተዳደር እንዲኖር ያግዛል፡፡

በሌላ በኩል አዲሱ የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ ከሚፈፀሙ ግብይቶች እና ከሌሎችም ዘመናዊ የግብይት መድረኮች ታክሱን መሰብሰብ የሚያስችል በመሆኑ መንግስት ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ሃብት ተገቢውን ድርሻውን እንዲያገኝ ያስችላል፡፡ በተጨማሪም መብቱ ከተቋቋመለት የህብረተሰብ ክፍል አልፎ የመክፈል ዓቅም ያለውን ሁሉ በመጥቀም ላይ ላለው የታክስ ነፃ መብት ገደብ በማበጀት መንግሥት ተገቢውን ታክስ እንዲሰበስብ ያስችላል፡፡


Comments

  1. Thank you for taking the time to provide such a well-rounded and informative explanation

    ReplyDelete

Post a Comment